“ቃል የምንገባቸውን ሁሉ በመፈፀም የተሰጠንን ተጨማሪ የኀላፊነት ጊዜ እንወጣለን ” ከንቲባ አዳነች አቤቤ

6

 

አዲስ አበባ: ሰኔ 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአዲስ አበባ ከተማ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በገዳም ሰፈር “የበጎነት መንደር” ግንባታ ተጀምሯል።

የአራዳ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ወንድሙ ዑመር በጎ ፈቃደኝነት በገንዘብ የማይገዛ፣ በደመወዝ የማይለካ ከአንጀት የሚሠጥ አገልግሎት ነው ብለዋል።

እየተጀመረ ያለው የክረምት በጎ ፈቃድ ሥራ የአረጋውያን እና አቅመ ደካሞች ክብር የሚታደስበት፣ እንባቸው የሚታበስበት የበጎነት እና የርህራሄ መንደር ግንባታ መኾኑን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር የኅብረተሰብ ተሳትፎ እና በጎ ፈቃድ አገልግሎት አሥተባባሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይመር ከበደ የበጎ ፈቃድ ሥራ ሰዎች ከጥልቅ ሰብዓዊነት አመለካከት ተነስተው ለሰው ልጆች የሚያበረክቱት የህሊና ስጦታ መኾኑን ተናግረዋል።

ባለፉት 8 ዓመታት በርካታ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች መሠራታቸውን ያስታወሱት ኀላፊው ከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ በጎ ፈቃደኞች መሳተፋቸውን እና 46ሺህ 461 ቤቶች ተገንብተው በቤተሰብ ደረጃ 207ሺህ 930 አቅመ ደካሞች እና አረጋውያን ተጠቃሚ መኾናቸውን ገልጸዋል።

በ2018 የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 5ሺህ 864 ቤቶች እንደሚገነቡ አንስተዋል። በቤተሰብ ደረጃ ከ38ሺህ በላይ ነዋሪዎች ተጠቃሚ ይኾናሉ። ለዚህም ከ55 ነጥብ 7 ቢሊዮን በላይ ብር ከበጎ ፈቃደኞች፣ ከባለሀብቶች፣ ከነዋሪዎች በጉልበት፣ በዓይነት እና በገንዘብ መሠብሠብ መቻሉን ጠቁመዋል።

የግንባታ ሥራውን ያስጀመሩት የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ሕዝቡ በምርጫው በሰጠው ድምጽ ምሥጋናቸውን አቅርበዋል። ቃል የምንገባቸውን ሁሉ በመፈፀም የተሰጠንን ተጨማሪ የኀላፊነት ጊዜ እንወጣለን ብለዋል።

ዘጠኝ ወለል ያላቸው ስምንት የመኖሪያ ሕንጻዎች፣ ሁለት ባለ አራተኛ ፎቅ የገበያ ማዕከላት፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች በመጀመሪያው ዙር እንደሚገነቡ እና “የገዳም ሰፈር የበጎነት መንደር” የዚህ አካል መኾኑን ተናግረዋል።

ከተማ አሥተዳደሩ ከመደበው በጀት በተጨማሪ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት፣ በላይነህ ክንዴ እና ከሌሎች ሀገር ወዳድ ባለሀብቶች እና ሕዝቡ ጋር ተባብረን ግንባታውን እውን እናደርጋለን ብለዋል።

#አሚኮ_ዜና #የበጎነት_ሥራ #አዲስ_አበባ #ኢትዮጵያ 🇪🇹

ዘጋቢ: ድልነሳ መንግሥቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article🕊በምዕራብ ጎንደር ዞን በርካታ የታጠቁ ኀይሎች የሰላምን አማራጭ እየተቀበሉ ነው።
Next articleበዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከ5 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ ነው።