
ባሕር ዳር: ሰኔ 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ( ኢዜማ) የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤት ይፋ መኾኑን ተከትሎ መግለጫ ሰጥቷል።
በመግለጫውም ምርጫው ከነእንከኖቹም ቢኾን በሰላም በመጠናቀቁ ፓርቲያችን እንኳን ደስ አለን ለማለት ይወዳል ብሏል።
ፓርቲው ለውድድር በቀረበባቸው ቦታዎች 13 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና 73 የክልል እና የከተማ ምክር ቤት ወንበሮችን በድምሩ 86 መቀመጫዎችን በማግኘት በሀገር አቀፍ ደረጃ ቀዳሚው ተፎካካሪ ፓርቲ ኾኖ ማጠናቀቁን አስታውቋል።
ይህንን ተጨባጭ ስኬት ላስመዘገቡ የፓርቲው ዕጩዎች፣ አባላት፣ ደጋፊዎች እና በሂደቱ በቅንነት ለተሳተፉ አካላት ሁሉ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፏል።
ፓርቲው ከቀጣዩ ምርጫ በፊት ባሉት ዓመታት ጠንካራ ጎኖቹን በማስቀጠል እና የነበሩበትን ክፍተቶች በስትራቴጂ እና ሌሎች አስፈላጊ ተግባራት በመሙላት ተጨባጭ የተፎካካሪ ፓርቲነት ሚናውን ጊዜ ሳያባክን የሚጀምረው ዛሬ መኾኑን ገልጿል።
ከዚህ ቀደም ስናደርገው እንደነበረ ሁሉ ብሔራዊ ጥቅሞችን በሚያሣኩ ጉዳዮች ከሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃይል ጋር በመተባበር የምንንቀሳቀስበት መኾኑም እንገልጻለን ብሏል።
መፎካከሪያ አጀንዳዎች ላይ ማኅበረሰባችንን በሚመጥን ጨዋነት ልዩነቶቻችንን እና ትችቶቻችንን እያቀረብን የጀመርነውን ጤናማ እና ዘመናዊ የፖለቲካ ባሕል የማዋለድ ተግባራችንን በተጠናከረ መልኩ እንቀጥላለን ነው ያለው።
ገዢ ኾኖ እንዲቀጥል ለተመረጠው ብልጽግና ፓርቲ እና የሕዝብ ውክልናን ላሳኩ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፏል።
አሸናፊው ፓርቲ ከዛሬ ጀምሮ ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ለመገንባት፣ ፍትሐዊ የፖለቲካ ምህዳርን ለሁሉም እኩል ተደራሽ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንዲሠራ፤ ለሀገር እድገትና ለውጥ ጠቃሚ ሀሳቦች ከማንኛውም ወገን ሊገኙ እንደሚችሉ በመረዳት አማራጭ ሃሳቦችን እንዲሰማ፤ ትችቶችን በሆደ ሰፊነት እያስተናገደ ሀገራችን የሚያስፈልጋትን ዴሞክራሲ በጋራ እንድንገነባ ጥሪ እናቀርባለን ብሏል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
