“ምርጫው ሕዝባችን ፈተናዎችን ተቋቁሞ በታሪክ የሚዘከር የአይበገሬነት ታሪክ የጻፈበት ነው” አብን

8
ባሕር ዳር: ሰኔ 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የምርጫ ውጤትን አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል።
በመግለጫውም ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሕዝባችን ለሰላም ሲባል ውድ ዋጋ ከፍሎ ያሸነፈበት ወሳኝ የታሪክ እጥፋት ነው ብሏል።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሕዝቡ ወደ ተሻለ የፖለቲካ እና የማኅበረ ኢኮኖሚ ምዕራፍ ለመሻገር ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየበት ውሳኔ ነው።
የተመዘገበው ስኬት የማኅበረሰባችን የአርቆ አሳቢነት ትሩፋት በመኾኑ ወሳኝ የታሪክ እጥፋት ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባም ነው።
ምርጫው ሕዝባችን ፈተናዎችን ተቋቁሞ በታሪክ የሚዘከር የአይበገሬነት ታሪክ የጻፈበት፣ ለዘላቂ ሰላም እና እድገት የሚበጅ የፖለቲካ ባሕል አሸናፊ ኾኖ እንዲወጣ ያደረገበት፣ በዋናነት የማኅበረ ፖለቲካ ግብረ-ገብ እሴቶች ተቃራኒ የኾኑ ጯሂና እኩይ ድምጸቶችን ማሸነፍ የቻለበት፣ ለሰላም ሲባል ዋጋ የመክፈል ቁርጠኝነት የታየበትና ዋጋ የተከፈለበት፣ ምርጫውን ለማደናቀፍ በቆሙ ኃይሎች አማካኝነት ዜጎች ሕይወታቸውን ያጡበት ክስተት ነበር፤ ያም ኾኖ ሕዝብን ማሸነፍ አይቻልምና ድሉ የሰላም ወዳዱ ሕዝብ ኾኗል ነው ያለው።
በዚህ መልኩ ሕዝቡ ከፍተኛ ጫናዎችን በመቋቋምና ዋጋ በመክፈል ጭምር ምርጫው ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል መድረክ መኾኑን ገልጿል። ቀጣይ ለሚመሰረተው መንግሥት ከፍ ያሉ የሕግ እና የፖለቲካ ግዴታዎች ተጥለውበታል እንደማለት ነው፡፡ ይህም ሰላም የማስፈን፣ የደኅንነት ዋስትና የማረጋገጥ፣ የልማት ተደራሽነትና ፍትሐዊነትን የማረጋገጥ ግዴታን የጠየቀበት መድረክ ኾኖ አልፏል ብሏል።
በተመሳሳይ በአማራ ክልል የትጥቅ እንቅስቃሴ እያደረጉ ላሉ ኃይሎችም ምርጫው ጠቃሚ መልዕክቶችን አስተላልፏል፡፡ አንድም የሕዝባችንን የፖለቲካ ተሳትፎ መብትና ነጻነቱን በኃይል የሚገፍ የጎበዝ አለቃዎች አዋጅና የተፈጸመውን ጥቃት እንደሚቃወመው ሕዝቡ አቋሙን ያሳወቀበት ነው፡፡ ሁለትም ለሰላማዊ የፖለቲካ ምህዳር ያለውን ፍላጎትና ለዚህም ዋጋ ለመክፈል በቁርጠኝነት እንደተነሳ በድርጊት የተደገፈ መልዕክት ያስተላለፈበት መድረክ ኾኗል፡፡
በዚህም “የአማራ ክልል ለመዋዕለ-ንዋይ ፍልሰት፣ ለፖለቲካዊ ተሳትፎ መቀጨጭ እና ለሰብአዊ ቀውስ የተዳረገው በክልሉ ከተፈጠረው የጸጥታ ቀውስ ጋር ተያይዞ ስለመኾኑ እና በተለይም ታሪካዊ ጠላቶች ይህንን አጋጣሚ እንደመልካም በመጠቀም የራሳቸውን እኩይ አጀንዳ ለማሳካት በሕዝባችን ላይ ሰፊ የማሳከርና የተቀናጀ የሽብር ዘመቻ እየፈጸሙ መኾኑን ሕዝባችን ጠንቅቆ የተገነዘበ መኾኑን እንረዳለን ብሏል።
ሕዝባችን ባሳለፋቸው በሳል ውሳኔዎች “የአማራ ክልል የቀውስ ፖለቲካ ተምሳሌት እንዲኾን፣ አማራ እንደ ሕዝብ ከሰላማዊ የፖለቲካ ትግል፣ ከተቋማዊነት ስርዓት እና ከማኅበረ ኢኮኖሚ ልማቶች እንዲነጠል ሁለንተናዊ ርብርብ ሲያደርጉ የነበሩ አካላትን አላማ በማክሸፍ አኩሪም-አስተማሪም ታሪክ ጽፏል ፍላጎቱንም ግልጽ አድርጓል።
ይህ ፈተናዎችን በጽናት የማለፍ ማኅበረሰባዊ ስኬት በማኅበረ ኢኮኖሚ ልማት እና በተቋም ግንባታ ሥራዎች ለመድገም ስርዓታዊ መደላድል የሚፈጥር እና ለሌሎች ድሎችም የሞራል መነቃቃትን የሚፈጥር ነው።
ምርጫው ለውጫዊ የኢትዮጵያ ጠላቶችም ተስፋ ያስቆረጠ ክስተት መኾኑን ገልጿል፡፡
ሕዝቡ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ባሳለፈው ውሳኔ አዲስ ለሚመሰረተው መንግሥት ከወትሮው የተለየ ኃላፊነት እና የማይደገም እድል እንደሰጠ አብን ይገነዘባል ብሏል። በመላው ሀገሪቱ ሕግና ስርዓት በማስከበር ለዜጎች የደኅንነት ዋስትናን የማረጋገጥ፣ በሃይማኖትና በብሔር ማንነት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን የማስቆም፣ ተንቀሳቅሶ የመሥራት ነጻነትን የማስከበር፣ ሀገራዊ ጥቅሞችን የማስጠበቅ ኃላፊነቶች ጊዜ የማይሰጣቸው የድህረ ምርጫ መንግሥት የቤት ሥራዎች መኾናቸውን አንስቷል።
ከሕዝብ እና ከሀገር ሕልውና ጋር ለሚያያዙ መሰረታዊ ኃላፊነቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት በሕዝቡ የተጣለበትን ታሪካዊ አደራ እንዲወጣ ጥሪ አቅርቧል፡ አዲሱ የሚመሰረተው መንግሥት የተጀመረውን ሀገራዊ ምክክር ከዳር በማድረስ፣ በሰላም ተቋማትን በማጠናከር እና የሰላም የኮሙዩኒኬሽንን ስርዓት ገቢራዊ በማድረግ አኩራፊ ኃይሎችን ወደ ፖለቲካ ምህዳሩ የማስገባት ጥረቶች አጠናክሮ እንዲቀጥል እንጠይቃለን ነው ያለው።
በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በትግራይ ክልሎች የሰላም አማራጭን እየተቀበሉ ያሉ አካላትን ከአቀባበል እስከ መልሶ ማደራጀት ባሉ ሂደቶች ተቋማዊ ስርዓት በመዘርጋት እየፈነጠቀ ያለውን የሰላም ጮራ ማስቀጠል የሚያስችሉ እርምጃዎች አጠናክሮ እንዲወስድ ጠይቋል።
የአማራ ክልልም የተቋረጡ ልማቶችን በማስቀጠል ላይ ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ እና የክልሉን ጸጋ በመለየት በቀሪዋ ኢትዮጵያ እየደረሱ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች እየተቀረጹ እንዲተገበሩ እና የሕዝባችን የመልሶ ግንባታ፣ እና የአዲስ ልማት ተጠቃሚነቱ በተጨባጭ እንዲረጋገጥ ጠይቋል፡፡
ተቆጥረው ያደሩ የሕዝባችንን መዋቅራዊ፣ የትርክት፣ የሕግና የፖለቲካ ጥያቄዎች በአግባቡ የሚስተናገዱበት ሀገራዊ የፖለቲካ ምህዳር እንዲሰናዳና በተግባር እንዲተረጎም እንጠይቃለን ነው ያለው።
አብን እንደ አንድ ሀገራዊ የፖለቲካ ተዋናይ ያለ ቅድመ ሁኔታ የሕዝባችንን ድምጽ የሚያከብርና በሕዝቡም ድምጽ የሚገዛ መኾኑን እያረጋገጠ፣ የማንኛውም በሕዝብ ስም የሚንቀሳቀስ የፖለቲካ ኃይል ቡድናዊ ፍላጎት ከሕዝቡ ፍላጎትና ውሳኔ ሊበልጥ እንደማይገባው ለማስታወስ ይወዳል ብሏል።
የወልቃይት እና ራያ ሕዝብ ማንነቱን ተገፎ ለዘመናት የሕይወት ዋጋ ጭምር እየከፈለ ሲታገል የነበረው ከግፍ አገዛዝ ተላቆ በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ራሱን የማስተዳደር መብቱን ለማስከበር እንደኾነ የሚታወቅ ነው፡፡ በምርጫ ሂደት የሥልጣን ባለቤትነት መብቱ እንዲረጋገጥለት እየጠየቀ ባለበት ሁኔታ ከመደበኛው የምርጫ መርሐ -ግብር ውጭ በመደረጉ የተነሳ የተፈጸመውን የመብት ጥሰት አብን በጽኑ ይቃወማል፤ በቀጣይም በጽኑ የሚታገልበት መድረክ መፆኑን ከወዲሁ አስምሮ ይገልጻል ብሏል።
የራያ ሕዝብ ለዘመናት በህወሃት ኃይሎች ሲደርስበት የነበረውን ግፍና ጭቆና ተቋቁሞ፣ ከግፍ አገዛዝ ተላቆ ራሱን በራሱ የማሥተዳደር መብቱን ለማስከበር አሁንም ድረስ ከፍተኛ መስዋዕትነት እየከፈለ መኾኑን ገልጿል።
የሕወሃት ኃይሎች በአካባቢው ላይ እያደረሱት ያለውን ሰብአዊ ጥሰት በጽኑ የሚያወግዝ መኾኑን አስታውቋል።
በድሕረ-ምርጫ የሚመሠረተው መንግሥት እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተጠቀሱት አካባቢዎች አፋጣኝ ምርጫ በማከናወን እና ነጻ የሕዝብ አሥተዳደር እንዲዋቀር በማገዝ ዋጋ ለተከፈለባቸው የመብት ጥያቄዎች መልስ እንዲሰጡ እንጠይቃለን ብሏል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleብልጽግና ፓርቲ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከፍተኛ ድምጽ በማግኘት ማሸነፉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
Next article“ጤናማ እና ዘመናዊ የፖለቲካ ባሕል የማዋለድ ተግባራችንን በተጠናከረ መልኩ እንቀጥላለን” ኢዜማ