በአማራ ክልል 30 ሺህ የሚጠጋ የቁም እንስሳት ለውጭ ገበያ ቀርቧል።

2

 

ጎንደር፡ ሰኔ 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ የቁም እንስሳት ኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከል እና የውጭ ግብይትን ለማሳለጥ ያለመ ውይይት ከባለድርሻ አካላት ጋር በጎንደር ከተማ አካሂዷል።

‎ውይይቱን የከፈቱት የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ አትክልት አሳቤ በበጀት ዓመቱ ከ29 ሺህ 700 በላይ የቁም እንስሳት ወደ ውጭ ሀገራት መላኩን አሳውቀዋል።

‎በዚህም ከ3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል ነው ያሉት።

“‎ክልሉ በቁም እንስሳት ሀብት የታደለ አካባቢ ነው” ያሉት ምክትል ኀላፊዋ ያለውን ጸጋ በአግባቡ መጠቀም ላይ ውስንነት አለ ብለዋል። ሕገ ወጥ ንግድን እና ኮንትሮባንድን በጋራ መከላከል እንደሚገባም አሳስበዋል።

‎ጤንነት እና ደኅንነታቸው የተጠበቀ እንስሳትን በማምረቱ ረገድ ሰፊ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሳ ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ነጋ ይስማው ናቸው።

‎በተለይም በእንስሳት ዘርፍ የሚሠራው ተግባር ግብ እንዲመታ ከንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ጋር በመቀናጀት የገበያ ትስስር እየተሠራ ነው ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ ከ26 ሺህ 600 በላይ እንስሳት በሕገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ መያዛቸውን የተናገሩት የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ የእንስሳት እና እንስሳት ተዋጽኦ ግብይት ዳይሬክተር ግዛቸው ክንዴ ናቸው። በተወሰደው እርምጃም ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ወደ መንግሥት ገቢ እንዲደረግ ኾኗል ነው ያሉት።

‎በክልሉ ሕገ ወጥ የቁም እንስሳት የሚዘዋወሩባቸው ቦታዎች ተለይተው የቁጥጥር ተግባራት እየተሠራ ነውም ብለዋል።

‎በቀጣይም ከዚህ በተሻለ ክትትል እና ቁጥጥር በማድረግ የውጭ ግብይትን ለማሳደግ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

‎የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ፍስሃ ሐጎስ በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ በሕገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የነበሩ ከ660 በላይ የቁም እንስሳት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተናግረዋል።

‎ከዚህም ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ወደ መንግሥት ገቢ ማስገባት ተችሏል ነው ያሉት።

‎ከ2 ሺህ 500 በላይ የቁም እንስሳት በሕገ ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ መያዛቸውን የተናገሩት ደግሞ የምዕራብ ጎንደር ዞን ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ጌትነት በሪሁን ናቸው።

‎ከዚህም ከ53 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ለመንግሥት ገቢ ተደርጓል ነው ያሉት።

‎በቀጣይ የተጀመረውን የእንስሳት ማቆያ ቦታ ለማጠናቀቅ እንደሚሠራም ተነስቷል።

#አሚኮ_ዜና #የቁም_እንሰሳት_ግብይት #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ

ዘጋቢ:- አዲስ አለማየሁ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ ያሉ የልማት ዕድሎችን መጠቀም ይገባል” አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር)
Next articleየኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ የውጤት ማሳወቂያ መርሐግብር እያካሄደ ነው።