“የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ ያሉ የልማት ዕድሎችን መጠቀም ይገባል” አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር)

4

 

ደባርቅ፡ ሰኔ 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ጎንደር ዞን አሥተዳደር ደባርቅ ከተማ በአካባቢው የልማት እና የሰላም ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት ተካሂዷል።

በመድረኩ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር) ጨምሮ ሌሎችም የክልል፣ የዞን እና የከተማ አሥተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች እና የወረዳው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ የአካባቢው ነዋሪዎች በዞኑ የመንገድ መሠረተ ልማት፣ የንፁህ መጠጥ ውኃ እና የኤሌክትሪክ አቅርቦት ችግርን መፍታት እንደሚገባ ተጠቁሟል።

ሰሜን ጎንደር ዞን የቱሪስት መዳረሻ መኾኑን ያነሱት ነዋሪዎች የልማት ጥያቄወችን በመመለስ ቱሪዝሙ ላይ መሥራት ይገባል ብለዋል።

ሰላምን ማረጋገጥ ቀዳሚ ነገር መኾኑን ያነሱት ነዋሪዎች ሰላምን ለማስፈን የበኩላቸውን እየተወጡ መኾኑን አንስተው አሁንም መንግሥት ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባው ተነስቷል።

የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዲያቆን ሸጋው ውቤ ዞኑን የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ እና ሰላምን ለማረጋገጥ እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል።

የመንገድ መሠረተ ልማት ሥራዎችን ለማሟላት ጥረት መደረጉንም ጠቁመዋል። ነገር ግን ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ በክልሉ ያለው የሰላም ሁኔታ ለመሠረተ ልማት ሥራዎች ፈታኝ መኾኑን ተናግረዋል።

የንፁህ መጠጥ ውኃ ተደራሽነት ችግርን ለመፍታት እየተሠራ ቢኾንም አሁንም ችግሩ መኖሩን አምነው በቀጣይ ችግሩን ለመፍታት በትኩረት እንደሚሠራ አመላክተዋል።

የኤሌክትሪክ ኀይል ችግርን ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ መኾኑን ጠቅሰው ችግሩን በጊዜያዊነት ለመፍታት ዘጠኝ የሶላር ፕሮጀክቶች እየተሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል። አሥተዳዳሪው ሰላምን ለማረጋገጥ በጋራ መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር) የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ ያሉ የልማት ዕድሎችን መጠቀም እንደሚገባ አመላክተዋል። ማኅበረሰቡም የልማቱ አጋዥ መኾን ይጠበቅበታል ብለዋል።

የክልሉ መንግሥት የመንገድ፣ የውኃ፣ የስልክ እና መሰል የልማት ጥያቄዎችን ለመፍታት ይሠራል ብለዋል።

መንግሥት ሰላምን ለማጽናት ቁርጠኛ አቋም አለው ያሉት ዶክተር አማኑኤል ሰላምን ለማረጋገጥ የጸጥታ አካላት እየሠሩ መኾኑን ገልጸዋል። በተደረገው ጥረትም አንፃራዊ ሰላም መገኘቱን ተናግረዋል። አሁንም ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የመንግሥትን የሰላም ጥሪ እንዲቀበሉ ማድረግ ከማኅበረሰቡ እንደሚጠበቅ አሳስበዋል ።

#አሚኮ_ዜና #የማኅበረሰብ_የሰላም_ውይይት #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ 🇪🇹

ዘጋቢ:- ቃልኪዳን ኃይሌ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article🇪🇹የኢትዮጵያን ትንሣኤ ሊያበስር ጫፍ የደረሰው የሀገራዊ ምክክር !
Next articleበአማራ ክልል 30 ሺህ የሚጠጋ የቁም እንስሳት ለውጭ ገበያ ቀርቧል።