🇪🇹የኢትዮጵያን ትንሣኤ ሊያበስር ጫፍ የደረሰው የሀገራዊ ምክክር !

4

 

ባሕር ዳር ፡ ሰኔ 14/2018 ዓ.ም(አሚኮ) ሀገራዊ ምክክር የዜጎችን እኩል ተሳትፎ በማረጋገጥ በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ያስችላል። ለዘመናት የዘለቁ የፖለቲካ እና የታሪክ ቅራኔዎች በውይይት እንዲፈቱ ዕድል ይፈጥራል።

🕊️የምክክር ባሕልን በማዳበር፣ ጥላቻን በይቅርታ፤ መከፋፈልን በአንድነት በመተካት ለጠንካራ ሀገር ግንባታ መሠረት ይጥላል። የጦርነትን አማራጭ በመዝጋት ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት፣ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን መደላድል ይፈጥራል።

ኢትዮጵያ ለዘመናት የተሸከመቻቸውን ውሥብሥብ አለመግባባቶች በዘላቂነት ለመፍታት በወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች።

✅ ለዚህ ዓላማ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎ በአሁኑ ወቅት ከመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሷል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ለመገናኛ ብዙኀን እንደገለጹት ባለፉት ዓመታት በተደረገው የምክክሩ ሂደት ለዋናው የምክክር ጉባኤ የሚያበቁ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል።

ሂደቱ አካታች፣ አሳታፊ እና ተዓማኒ እንዲኾን በተደረገው ጥረት በመላ ሀገሪቱ 1 ሺህ 234 ወረዳዎችን ማሳተፍ እንደተቻለ አስታውቀዋል። በዚህም የተሳካ አጀንዳ ማሠባሠብ መቻሉን አረጋግጠዋል።

💪በሂደቱ ያጋጠሙ መሠናክሎችን በጥበብ በማለፍ ወሳኝ እና የመጨረሻ ወደኾነው የምክክር ጉባኤ ተሸጋግረናል ነው ያሉት።

በውጤቱም በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት እንዲሻሻል፣ መተማመን እንዲፈጠር ለማድረግ ተስፋ የተሰነቀበት ስለመኾኑም አብራርተዋል።

ለዘመናት እየተንከባለሉ የመጡ ውስጣዊ ችግሮች እንዲፈቱ፣ መተማመን የሰፈነበት አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት እንዲገነባ፣ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ፣ ጠንካራ እና ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥት እንዲገነባ ጽኑ መሠረት የሚጥል ስለመኾኑም አስገንዝበዋል።

🤝በምክክር ጉባኤው የኢትዮጵያ ሕዝቦች በተወካዮቻቸው አማካኝነት ተከባብረው፣ ተደማምጠው እና ተመካክረው በመግባባት የሚያቀርቧቸው ምክረ ሀሳቦች በተግባር ተተርጉመው ኢትዮጵያ ወደ አዲስ የሰላም እና የዕድገት ምዕራፍ እንድትሸጋገር የሚያስችል ስለመኾኑም አመላክተዋል።

በጉጉት የሚጠበቀው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ከሐምሌ 8/ 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሦሥት ተከታታይ ሳምንታት በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ዋና ኮሚሽነሩ ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው።

#አሚኮ_ዜና #ሀገራዊ_ምክክር #ኢትዮጵያ 🇪🇹

ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢቦላ በአውሮፓ ወይም በአሜሪካ ቢኾን ኖሮ እስካሁን ክትባት እና መድኃኒት ይሠራለት ነበር” ዶክተር ዣን ካሴያ
Next article“የልማት ጥያቄዎችን ለመመለሾ ያሉ የልማት ዕድሎችን መጠቀም ይገባል” አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር)