ሕገ ወጥ የአፈር ማዳበሪያ ዝውውርን ለመከላከል በቅንጅት እየተሠራ ነው።

4

 

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የግብዓት አቅርቦትን በወቅቱ እና በፍትሐዊነት ለአርሶ አደሮች ማድረስ ወሳኝ ነው። የአማራ ክልል ግብርና ቢሮም የማዳበሪያ አቅርቦት በወቅቱ እና በፍትሐዊነት ለማሰራጨት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አስታውቋል።

ይሁን እንጂ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች እንደሚናገሩት ማዳበሪያ በሕገ-ወጥ ነጋዴዎች እጅ በመግባቱ ምክንያት ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እያጋጠማቸው ነው። አርሶ አደሮቹ ይህ ችግር በቀጣይ ለሚዘሩ ሰብሎች መስተካከል እንዳለበትም ጠይቀዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የግብርና ግብዓት እና ሜካናይዜሽን ዳይሬክተር ሙሽራ ሲሳይ የዘንድሮው የ2018/19 የክረምት ወቅት የማዳበሪያ አቅርቦት ካለፈው ዓመት አንጻር የተሻለ መኾኑን ገልጸዋል።
​እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ በዘንድሮው የክረምት ወቅት ከ8 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዶ እስካሁን ወደብ የደረሰው ከ4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ነው ብለዋል።

ከዚህ ውስጥ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል የሚኾነው ወደ ክልሉ የገባ መኾኑን ነው የተናገሩት። ከደረሰው ማዳበሪያ ውስጥም የከረመውን ጨምሮ ከ3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ለአርሶ አደሮች መሰራጨቱን አስረድተዋል።

በሁሉም አካባቢዎች ፍትሐዊ እና ወቅታዊ ስርጭት እንዲኖር አስቀድሞ ዝግጅት መደረጉን የተናገሩት ዳይሬክተሯ የማዳበሪያ አቅርቦት ክፍተት ችግር የነበረባቸውን የሰሜን እና ደቡብ ጎንደር ዞኖችን ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። በተለይም አርሶ አደሮች በሚዘሩት የመሬት መጠን ልክ ተደራሽ እንዲኾን ጥረት እየተደረገ መኾኑን ነው ያስረዱት። አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ ይሠራልም ነው ያሉት።

በሕገ-ወጥ መንገድ የሚፈጸም የግብዓት ዝውውርን ለመቆጣጠር ክትትል የሚያደርግ እስከ ቀበሌ ድርስ ግብረ-ኀይል ተቋቁሞ እየተሠራ ይገኛልም ብለዋል። በሕገ-ወጥ መንገድ የተያዘ ማዳበሪያ በሕግ አግባብ ተይዞ በመደበኛ ዋጋ ለአርሶ አደሮች እንዲቀርብ እንደሚደረግም ተናግረዋል።

​ቁጥጥሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያረጋገጡት ዳይሬክተሯ ማኅበረሰቡ ይህንን ሕገ-ወጥ ድርጊት ሲመለከት በወቅቱ ጥቆማ በመስጠት እንዲተባበር አሳስበዋል። ከወደብ የማጓጓዝ ሥራውም የዕቅዱን ግብ ለማሳካት እስከ ሐምሌ 2018 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል።

#አሚኮ_ዜና #የግብዓት_ሥርጭት_ሥራ #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ

ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የአዲስ አበባ ከተማ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ለሌሎች ዓለማቀፍ ከተሞችም አስተማሪ ነው” አቶ አገኘሁ ተሻገር