
አዲስ አበባ፡ ሰኔ 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 8ኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር “ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ተጀምሯል።
በከተማዋ በዘንድሮ ዓመት 6 ሚሊዮን ችግኝ እንደሚተከል የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል።
ባለፉት ሰባት ዓመታት በአዲስ አበባ ከተማ 90 ሚሊዮን ችግኝ ተተክሏል ያሉት ከንቲባዋ ይህ እንዲጸድቅ እና ለፍሬ እንዲበቃ ከፍተኛ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል።
“የከተማዋ የደን ሽፋን ከነበረበት 2 ነጥብ 4 በመቶ ወደ 24 በመቶ ከፍ ማለቱን እና የምንተክለው ተስፋችን እና ምግባችን ነውና ተባብረን እንትከል” ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
በአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ የተገኙት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በሀገሪቱ የአካባቢ ጥበቃ ተቋማዊ ኾኖ እየተሠራ መኾኑን አስታውሰዋል።
በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ እየተሠራ ያለው የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን በዓለም አቀፍ ደረጃ ኹሉ አስተማሪ ነው ብለዋል።
ይህ ተግባር የከተማዋን ተወዳዳሪነት ከፍ የሚያደርግ በመኾኑ፣ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ለትውልድ የሚሻገር ሥራ መሥራት ይጠበቅበታል ነው ያሉት።
በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ሌሎች የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች እና የከተማዋ ማኅበረሰብ ተሳትፏል።
#አሚኮ_ዜና #የአረንጓዴ_አሻራ_ሥራ #በአዲስ_አበባ #ኢትዮጵያ
ዘጋቢ፦ አየለ መስፍን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
