የ403ኛ ኮር በአስቸጋሪ ወቅትም ፈተናን ተቋቁሞ በጽናት በማለፍ አርዓያነት ያለው ተግባር መፈጸም የቻለ ሠራዊት ነው።

3

 

ጎንደር፡ ሰኔ 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገር መከላከያ ሠራዊት 403ኛ ኮር በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ከሕዝብ ጋር በአንድነት ላስመዘገበው አንፀባራቂ የጀግንነት ተጋድሎ መታሰቢያ በሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ከተማ በፓናል ውይይት እና በልዩ ልዩ መርሐ ግብሮች ዕለቱን እያከበረ ነው።

በመርሐ ግብሩ የሀገር መከላከያ ሠራዊት መሪዎች፣ የክልል እና የዞን የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

በፓናል ውይይቱ ላይ “ዝክረ ጭና የሰማዕታት መታሰቢያን” የሚያወሱ ሀሳቦች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት የመገናኛ እና ኢንፎርሜሽን ሲስተም ዋና መምሪያ ኀላፊ ሌተናል ጄኔራል መሠለ መሠረት ጀግንነት እና ጽናትን ከአያት አባቶቻቸው የወረሱት የ403ኛ ኮር አባላት ከተለያዩ የሠራዊቱ ክፍሎች እና ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በመኾን በወቅቱ ያስመዘገቡትን ደማቅ ጀግንነት አድንቀዋል።

በሰሜኑ የኅልውና ዘመቻ ወቅት ተካሂዶ በነበረው እልህ አስጨራሽ ፍልሚያ 403ኛ ኮር በመስዋዕትነት የደመቀ የተጋድሎ ታሪክ የፃፈበት ስፍራ ጭና መኾኑንም አስታውሰዋል።

ኮሩ በኢትዮጵያዊነት እና በአንድነት ስሜት ለሀገር ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለ የሀገር አለኝታ መኾኑንም ገልጸዋል።

በሀገር መከላከያ ሠራዊት የምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል አማረ ባህታ ኮሩ ከተመሠረተበት የሰሜኑ ጦርነት ወቅት ጀምሮ የሀገርን ሰላም በማስከበር ተልዕኮዎች ላይ በውጤታማነት መሳተፉን ገልጸዋል።

በአስቸጋሪ ወቅትም ፈተናን ተቋቁሞ በጽናት በማለፍ አርዓያነት ያለው ተግባር መፈጸሙንም አስረድተዋል።

የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዲያቆን ሸጋው ውቤ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት በጭና አካባቢ በተከፈለው የሕይወት መስዋዕትነት ሀገርን ከጥፋት፣ ወገንን ከጥቃት ማዳን ተችሏልም ብለዋል።

ዘላቂ ሰላም እና ልማትን ለማረጋገጥ ማኅበረሰቡ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ከክልሉ የጸጥታ መዋቅር ጎን በመሰለፍ ድጋፉን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ገልጸዋል።

#አሚኮ_ዜና #የመከላከያ_ሠራዊት_የሰላም_ማስከበር_ተልዕኮ #ኢትዮጵያ 🇪🇹

ዘጋቢ:- ቃልኪዳን ኃይሌ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ መልእክት!