በአማራ ክልል የሌማት ትሩፋት የወጣቶችን ሕይዎት እየቀየረ ነው።

5

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ወጣት መሐመድኑር ይማም በስደት በአረብ ሀገር ለረጅም ጊዜ ቆይቷል። አኹን ላይ በከሚሴ ከተማ በዶሮ እርባታ ሥራ ተሰማርቶ ይገኛል።

ወጣቱ ሠርቶ መለወጥን በመምረጥ በጀመረው ሥራ በቀን ከ2 ሺህ 200 በላይ እንቁላል በማቅረብ ተጠቃሚ መኾኑን ገልጿል።

ሌላኛው ወጣት አክሊሉ አስማረ በከብት ማድለብ ተሰማርቶ ተጠቃሚ መኾኑን ተናግሯል። በባለሙያዎች በኩልም የተለያዩ ሙያዊ ድጋፎችን እያገኘ ስለመኾኑ ይናገራል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት መምሪያ ኀላፊ ሐሰን ሰይድ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ ውጤታማ የሌማት ቱርፋት ሥራዎች ተሠርተዋል።

ለአብነትም:-

🐂 ከ190 ሺህ እንስሳት በላይ ማድለብ ተችሏል።
🐂 ከ7ሺህ 700 ቶን በላይ ስጋ ለገበያ ቀርቧል።
🥚 ከ35 ሚሊዮን በላይ እንቁላል በማምረት ለገበያ ቀርቧል።
🐝 ከ1ሺህ 400 በላይ የሽግግር ቀፎዎችን በማዘጋጀት ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
🍯 ከ430 ቶን በላይ የማር ምርት ተገኝቷል ብለዋል።

የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሣሳ ሃብት ልማት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ሀብታሙ ሁነኛው ለአሚኮ እንደገለጹት ፤ ቢሮው በብሔረሰብ አሥተዳደሩ እስከ ወረዳ እና ቀበሌ ድረስ በመውረድ ልዩ ድጋፍ እና ክትትል ሲያደርግ ቆይቷል።

በተደረገው ድጋፍም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተጨባጭ ሥራዎች እየተከናወኑ ስለመኾኑ ገልጸዋል።

ለአብነትም በአርጡማ ፋርሲ፣ በባቲ፣ በደዋ ጨፋ እንዲኹም በከሚሴ ከተማ ዙሪያ ወረዳዎች በዓሣ እርባታ በከብት ማድለብ፣ በማር እና በዶሮ እርባታ የሕዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ሥራዎች መሠራታቸውን አብራርተዋል።

በአማራ ክልል በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር 157 ሺህ ወጣቶች ተጠቃሚ መኾን ችለዋል። መርሐ ግብሩ የወጣቶችን ሕይዎት እየቀየረ እንደሚገኝም አብራርተዋል። በክልሉ የሌማት ትሩፋት ሥራዎችን በውጤታማነት ለማስቀጠል መልካም ተሞክሮዎችን የማሥፋት፤ የሙያ፣ የቴክኖሎጂ እና የሥልጠና ድጋፎችም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመላክተዋል።

#አሚኮ_ዜና #የሌማት_ትሩፋት #ከሚሴ #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ

ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየ403ኛ ኮር በአስቸጋሪ ወቅትም ፈተናን ተቋቁሞ በጽናት በማለፍ አርዓያነት ያለው ተግባር መፈጸም የቻለ ሠራዊት ነው።