በአፍሪካ የመጀመሪያ የኾነው የኤ.አይ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ እውን ሊኾን ነው።

6

 

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (ኤ.አይ) የዓለምን ሁለንተናዊ ገጽታ የቀየረ የዘመኑ ክስተት ኾኗል። ተለዋዋጭ በኾነው የዓለም አቀፋዊ ሁነት ውስጥ የኤ አይ ቴክኖሎጂ ተጽዕኖ ከፍተኛ እየኾነ መጥቷል። 🌍

በኤ.አይ ዙሪያ የሚደረግ ኢንቨስትመንት የወደፊቱን የዲጂታል ሉዓላዊነት የማረጋገጫ ቁልፍ መንገድ ስለመኾኑም የዘርፉ ምሁራን ይተነትናሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተለያየ ወቅት እንደገለጹት ኢትዮጵያም ለአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ልዩ ትኩረት ሰጥታለች። በተለይም ወጣቶችን ነገ ለሚጠብቃቸው ውድድር ዛሬ ላይ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግም ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያ በቴክኖሎጅው ዘርፍ ትውልድ ላይ ለመሥራት ታሳቢ ያደረገ በዓለም ሁለተኛውን በአፍሪካ ደግሞ የመጀመሪያ የኾነውን የኤ አይ ዩኒቨርሲቲ በአዲስ አበባ እየገነባች መኾኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

በአንድ ዓመት ውስጥም ተመርቆ ሥራ እንደሚጀምር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማረጋገጣቸው ይታወሳል። ይህም በሀገሪቱ የቴክኖሎጂ ሽግግር ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት እርምጃ ነው።

ዩኒቨርሲቲው ሥራ ሲጀምር ለሁሉም የአፍሪካ ሀገራት የኤ አይ ስኮላርሽፕ የትምህርት ዕድል እንደሚፈጥር እና ለአፍሪካውያን ትልቅ የቴክኖሎጂ መሠረት ኾኖ እንደሚያገለግል ጠቁመዋል። 🎓🤝

📌የሚገነባው የኤ አይ ዩኒቨርሲቲ ምን ፋይዳ ይዞ ይመጣ ይኾን?

👉 የሀገር በቀል ዕውቀት ግንባታ 🧠

🤖 የኤ አይ ዩኒቨርሲቲ መቋቋም የውጭ ሀገራትን የቴክኖሎጂ ጥገኝነት በመቀነስ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። የሀገር በቀል ዕውቀትን እና ፍላጎትን መሠረት ያደረጉ የኤ አይ መፍትሄዎችን ለማውጣት፣ በዘርፉ የሠለጠነ እና የረቀቀ የሰው ኀይል በሀገር ውስጥ ለማፍራት ያስችላል።

👉 ለቴክኖሎጂ ሽግግር🔄📡

ዩኒቨርሲቲው ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚኾኑበትን የዳታ ሳይንስ፣ የሮቦቲክስ፣ የማሽን ለርኒንግ እና የኮምፒውቲንግ ክህሎት እንዲጨብጡ ያስችላል። በዚህም ኢትዮጵያን የአፍሪካ የቴክኖሎጂ ማዕከል ያደርጋታል።

👉ለቁልፍ የልማት ዘርፎች ዕድገት ማሳለጫ📈

🌾በግብርናው ዘርፍ የአፈርን እርጥበት ለመለካት፣ የሰብል በሽታዎችን አስቀድሞ ለመለየት፣ የአየር ንብረት መዛባትን ለመተንበይ የሚያስችሉ የኤ አይ ስልተ-ቀመሮችን ወደ ተግባር በማስገባት ዕድገትን ለማሳለጥ እና የሀገሪቱን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ትልቅ አቅም ይፈጥራል።

🩺በጤናው ዘርፍ የሕክምና አገልግሎት ተደራሽ ባልኾነባቸው አካባቢዎች በሽታዎችን በምስል እና በዳታ ትንተና ፈጥኖ ለመለየት፣ በመሠረተ ልማት እና በተደራጀ ሎጀስቲክስ ለመምራት መደላድል ይፈጥራል።

👉 የምጣኔ ሀብት እና የፈጠራ አቅምን ለማሳደግ

ዩኒቨርሲቲው ከትምህርት ባለፈ የቴክኖሎጂ ተሰጥኦ ያላቸው ወጣቶች ሀሳባቸውን ወደ ሥራ የሚቀይሩበት ማዕከልም እንደሚኾን ይጠበቃል።

የዲጂታል ኢኮኖሚውን የሚያነቃቁ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የሚፈልቁበት ምኅዳርን ይፈጥራል። ይህም ለበርካታ ወጣቶች የተለየ የሥራ ዕድል ይዞ የሚመጣ ነው።

#አሚኮ_ዜና #የኤ አይ_ግንባታ #ኢትዮጵያ 🇪🇹

ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article📱🇪🇹ኢትዮጵያ በዲጂታሉ ዓለም ወደ ላቀ ደረጃ እየተሻገረች ነው።
Next articleየምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ መልእክት!