
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ዓለም ከደረሰበት የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዕድገት ለመድረስ በርካታ አድራሽ የቴክሎጂ መንገዶችን እያማተረች ነው። ዲጂታል 2025ን ዕውን ለማድረግ ዜጎቿን በኮደርስ፣ አገልግሎቷን በአንድ መሶብ አገልግሎት፣ በፋይዳ እና በሳይንስ ሙዚዬም እያገዘች ጉዞዋን ቀጥላለች።
ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመኾን ሁሉም የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሚገኙበትን የሳይንስ ሙዚየም መስከረም 24/2015 ዓ.ም በይፋ ከፍታለች።
የማያቋርጥ የከፍታ ጥረትን እና ምኞትን እንዲያሳይ ተደርጎ የተገነባው ሕንጻው በውስጡ በቴክኖሎጂ ጥግ ላይ ከደረሱ ሀገራት ተርታ የሚያሰልፉ የቴክኖሎጂ ክፍሎችን ይዟል።
በሙዚየሙ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ማሽኖችን ከማሠልጠን ጀምሮ በጤና፣ በፋይናንስ፣ በግብርና እና በቋንቋ ዘርፎች ላይ ያመጣውን የላቀ ለውጥ እና የወደፊት ዕድሎችን በተግባር የሚያሳዩ ቴክኖሎጂዎች እንደሚገኙ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።
ሀገሪቱ ቀደምት ጥበቦችን ከዘመናዊ ዲጂታል መሣሪያዎች ጋር በማጣመር በ’ስማርት ግብርና’ እራሷን ለመቻል እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የምታደርገውን ጥረት ይዳስሳል።
የመጭው ዘመን የኀይል አቅርቦት ያለውን የውኃ እና የኀይል ጉዞ፣ የሀገሪቱን ታሪካዊ እና ዘመናዊ የአቪዬሽን ሚና እንዲሁም ከትንሿ ሕዋስ እስከ ከዋክብት ያለውን ሰፊ የሳይንስ ዕውቀት ያስቃኛል።
ማዕከሉ አዳዲስ ምናባዊ ሀሳቦች ወደ ፈጠራ ግኝት የሚቀየሩበት እና የሀገሪቱን ብሩህ ተስፋ የሚያሰርጽ የዕውቀት ማማ ኾኖ እያገለገለ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ማዕከሉን አስመልክቶ በተለያዩ ጊዜያት ባደረጉት ንግግር በሳይንስ ሙዚየም የሚገኙት ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በተለይ ሕጻናት እና ወጣቶች ነገሮችን በእጃቸው እየነኩ በተግባር እንዲማሩ የሚያደርግ መኾኑን ተናግረዋል። ይህ ዕድል ሕጻናት የቴክኖሎጂ ተከታይ ብቻ ሳይኾኑ ፈጣሪ እንዲኾኑ እና የነገ ማንነታቸውን እንዲገነቡ እንደሚያግዝም ተናግረዋል።
#አሚኮ_ዜና #ሳይንስ_ሙዚየም #ኢትዮጵያ 🇪🇹
ዘጋቢ፦ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
