የፋይዳ መታወቂያ የኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚ ልህቀትን እያረጋገጠ ነው !

1

 

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በታሪኳ ዓይታው በማታውቀው የዲጂታላይዜሽን አብዮት ውስጥ ትገኛለች። የዚህ ታላቅ ሽግግር ማሳለጫ ደግሞ የፋይዳ ዲጂታል ብሔራዊ መታወቂያ ነው። ከባንክ አሠራር ዘመናዊነት እስከ አርሶ አደሩ የብድር አገልግሎት፤ ከኢ-ኮሜርስ ዕምነት ግንባታ እስከ ኮንትሮባንድ መከላከል ድረስ ፋይዳ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ መዋቅር በአስገራሚ ሁኔታ ቀይሮታል።

የፋይዳ ዲጅታል ብሔራዊ መታወቂያ የኢትዮጵያን ዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግር ዕውን ለማድረግ እና መላው ኢትዮጵያውያንን በፋይናንስ ሥርዓቱ ውስጥ ለማካተት የተዘረጋ የዲጂታል ሥርዓት ነው። የዜጎችን ማንነት በታማኝነት፣ በደኅንነት እና በአንድ ማዕከል ለማረጋገጥም ያስችላል። በዚህ ሂደት የቆየውን የኢኮኖሚ መዋቅር ወደ ዘመናዊ ሥርዓት ለማሸጋገር ከፍተኛ ሚና እየተጫወተም ይገኛል።

💳✨ ዲጅታል መታወቂያ ለፋይናንስ ዘርፍ መነቃቃት፥

የፋይዳ መታወቂያ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ ትልቅ ለውጥ እያስመዘገበ መኾኑ ተነግሯል። ባንኮች ደንበኞቻቸውን ከፋይዳ ቁጥር ጋር እንዲያገናኙ ግዴታ እንደተጣለባቸው የሚታወስ ነው። ይህ አሠራር በባንኮች እና በደንበኞቻቸው መካከል ያለውን ማንነት ፍጹም ዕውነተኛ ያደርጋል። ወረቀት አልባ እና ዘመናዊ የባንክ ሥርዓትን ለመገንባት እያገዘ እንደኾነም ነው የተነገረው።

የሞባይል ገንዘብ አቅራቢዎች ደንበኞችን ለመመዝገብ እና ለማረጋገጥ የሚያወጡትን ጊዜ እና ገንዘብ በከፍተኛ ደረጃ ቀንሶላቸዋል።

🛍️🔒 ዲጅታል መታወቂያ ለዲጂታል ክፍያዎች እና ለኢ-ኮሜርስ መተማመን፦

ኢ-ኮሜርስ ወይም የበይነ መረብ ንግድ እንዲያድግ በገዢ እና በሻጭ መካከል ፍጹም ዕምነት መኖር አለበት። ፋይዳ በበይነ መረብ ንግድ ላይ የሚፈጠሩ የማጭበርበር ተግባራትን ሙሉ በሙሉ ያስቀራል። የኤሌክትሮኒክስ ክፍያዎች በቀጥታ ከተረጋገጠ ግለሰብ ማንነት ጋር በማገናኘትም የፋይናንስ ደኅንነት ሥጋትን በእጅጉ እንደሚቀንስ ነው ባለሙያዎች ያስረዱት።

🌾🚀 ዲጅታል መታወቂያ ለግብርና እና ለገጠር ትራንስፎርሜሽን መሳለጥ፦

የኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ለከተማ ብቻ የመጣ ቴክኖሎጂ ሳይኾን ገጠሩንም የሚያዳርስ ነው። በሀገሪቱ በርካታ አርሶ እና አርብቶ አደሮች የፋይዳ ዲጅታል መታወቂያ አውጥተው የዲጂታል ጉዞው አካል ኾነዋል። በዚህም
ግብዓት ያለምንም ማጭበርበር እንዲደርሳቸው እና ከመደበኛ ባንኮች የብድር እና የኢንሹራንስ አገልግሎት እንዲያገኙ የፋይዳ መረጃ አያያዝ ሥርዓት ትልቅ በር ከፍቶላቸዋል።

🔍🛡️ ዲጂታል መታወቂያ ለግልጽነት እና ኮንትሮባንድ/ማጭበርበርን ለመከላከል፦

ሀገሪቱ ከፍተኛውን በጀት ከምትሠበሠሥብባቸው መንገዶች አንዱ በኾነው ግብር የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ከፍተኛ ጠቀሜታን ይሰጣል። የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ የግብር አሠባሠብን ግልጽ እና ቀልጣፋ ማድረጉ ነው የሚነገረው።ዲጂታል መታወቂያ በጣት አሻራ፣ በዐይን እና የፊት ገጽታ መረጃዎች ላይ የተመሠረተ በመኾኑም ሕገ-ወጥ የንግድ ሥራዎች ወይም የፋይናንስ ማጭበርበሮች እንዳይፈፀሙ ሙሉ በሙሉ እየተከላከለ ነውም ተብሏል።

የፋይዳ ዲጂታል ብሔራዊ መታወቂያ ካርድ ብቻ ሳይኾን ኢትዮጵያን ወደ ዘመናዊ፣ ግልጽ እና ሁሉን አቀፍ የዲጂታል ኢኮኖሚ ሥርዓት የሚያሸጋግር የዕድገት ቁልፍ ተደርጎ ይወሰዳል።

#አሚኮ_ዜና #ዲጂታል_መታወቂያ #ኢትዮጵያ 🇪🇹

ዘጋቢ፦አድኖ ማርቆስ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article🔐ከችግር ወደ መፍትሔ መሻገሪያ 🇪🇹የኢትዮጵያ ታላቁ የምክክር ጉባኤ !
Next articleየሳይንስ ሙዚየም የኢትዮጵያ ዲጂታል ከፍታ አብሳሪ ነው።