🔐ከችግር ወደ መፍትሔ መሻገሪያ 🇪🇹የኢትዮጵያ ታላቁ የምክክር ጉባኤ !

5

 

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 🇪🇹ኢትዮጵያውያን ሉዓላዊነታቸውን የሚዳፈር፣ የሀገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ ክብር ለማዋረድ የሚመጣ ጠላትን በአንድነት ክንድ፣ በአብሮነት ጋሻ፣ በወንድማችነት ጦር ጠላትን በነቂስ ወጥተው ያሸንፋሉ።

በሀዘን፣ በደስታ፣ በችግር ወቅትም በአብሮነት ተቀምጠው ይመክራሉ፣ ደስታን ይጋራሉ፣ ሀዘንን ይካፈላሉ፣ በአንድነት ለችግሮቻቸው መፍትሔን ያስቀምጣሉ።

🗓ይህ ታሪካቸውን ለማስቀጠል ሐምሌ 8/2018 ዓ.ም ስለሀገራቸው ሊመክሩ፣ ስለ አንድነታቸው ሊመሰክሩ፣ ስለ ዘላቂ ወንድማማችነታቸው በኅብረት🤝 ውል ሊያስሩ ታላቅ ቀጠሮን ይዘዋል።

ላለፉት አራት ዓመታት ዝግጅት ሲደረግበት የቆየው ሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ 4 ሺህ ያህል ተሳታፊዎችን በማካተት ለሦሥት ተከታታይ ሳምንታት በአዲስ አበባ ይደረጋል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ሀገራዊ ምክክር ኮምሽኑ ሐምሌ 8/2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ጉባኤው እጅግ መሠረታዊ በኾኑ ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ በሰለጠነ መንገድ ለመመካከር እና ዘላቂ መግባባት ላይ ለመድረስ ያስችላል ብለዋል።

ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ውስጣዊ ችግሮቻችን ተፈትተው ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ያስችላል ነው ያሉት። ጠንካራ ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ጽኑ መሠረት እንደሚጥልም በወቅቱ አብራርተዋል።

በሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ላይ ኢትዮጵያውያን ይመከርባቸው ብለው ያነሷቸው ጉዳዮች በሙሉ በአጀንዳነት የተያዙ ናቸው።

ይህ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ውይይት የኢትዮጵያ የውስጥ ችግርን የሚቀርፍ፣ ዘላቂ ሰላም እንዲኖር የሚያስችል፣ ዜጎች አንድነታቸውን ይበልጥ እንዲያጠናክሩ የሚረዳ፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ በማኀበራዊ እና በኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ቀዳሚ እንድትኾን የሚያስችል ነው።

ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በኢኮኖሚ ተወዳዳሪ እንድትኾን ማኅበረሰቡ ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ድጋፍ በማድረግ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች ስለ ሀገር በአብሮነት እና ኢትዮጵያ በምትታወቅበት ባሕላዊ እሴት በቅንጅት በመምከር 👨‍👨‍👧‍👦ለትውልድ የሚበጅ፣ ሀገርን የሚያሻግር የመፍትሔ ሀሳብን ማፍለቅ ይጠበቅባቸዋል።

#አሚኮ_ዜና #ሀገራዊ_ምክክር #ኢትዮጵያ 🇪🇹

ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በቴክኖሎጅ ዘርፍ በአጭር ጊዜ ያመጣነውን ለውጥ ለአፍሪካ ምሳሌ ኾነን ዓድዋን ዳግም በልማት እናሳያለን” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)