“በቴክኖሎጅ ዘርፍ በአጭር ጊዜ ያመጣነውን ለውጥ ለአፍሪካ ምሳሌ ኾነን ዓድዋን ዳግም በልማት እናሳያለን” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

7

 

አዲስ አበባ፡ ሰኔ 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በአፍሪካ ቀዳሚ የተቀናጀ የዲጂታል አገልግሎት መተግበሪያን መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መተግበሪያውን የመረቁት ‘’ዲጂታል ለልህቀት’’ በሚል ስያሜ በተዘጋጀው ጉባኤ ላይ ነው።

መተግበሪያው በተለያዩ ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችን በአንድ መድረክ የሚያጣምር እንደኾነም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

የአንድ ‎መሶብ አገልግሎት በርካታ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን መያዙን እና ጊዜን ቆጥቦ ለተጨማሪ ውጤታማነት እና በሀገር ደረጃ ደግሞ ትርፋማ እያደረገ የሚገኝ የኢኮኖሚ መሠረተ ልማት ነው ብለዋል።

የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ለእጅ መንሻ የሚጠየቁበትን ክፉ ልማድ እና ሌብነት በማስቀረት የዜጎችን ደስታ በመጨመር ዉጤታማ ያደርጋል ነው ያሉት።

የአንድ መሶብ አገልግሎት በቴክኖሎጅ የዘመነ አገልግሎት በሀገሪቱ የዓመታት እና ተደጋጋሚ የነበረ የመንግሥት ስብራትን እና የተቋም ግንባታ ነጠላዊ አካሄድን በማስቀረት የተሰናሰለ የሚናበብ አንድ ተቋም መገንባት አስችሏል ሲሉ ተናግረዋል።

መንግሥት በዘመኑ ተወዳዳሪ በመኾን ብልጽግናን ለማረጋገጥ ያለመውን ራዕይ ለማሳካት ከአምስቱ ቁልፍ ሴክተሮች አንዱ ቴክኖሎጂን በማድረግ ዛሬ ላይ እየተመዘገቡ ባሉ ውጤቶች እየተገለጠ ነው ብለዋል።

በዘገየነው ልክ ሳይኾን ተሽቀዳድመን በሚገባን ተርታ ለመቆም ቴክኖሎጅ ወሳኝ መኾኑን በመገንዘብ ኢትዮጵያ እጅግ አስደናቂ ስኬቶችን አስመዝግባለች ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

በአንድ ዓመት ውስጥ የአንድ መሶብ አገልግሎት ከአንድ ወደ ሰባ ቅርንጫፎች ማሳደግ ተችሏል፣ ከሦሥት ወር ባጠረ ጊዜ አገልግሎቱን ይበልጥ ዘመናዊ አድርጎ ለሰዎች በማቅረብ ወደ አውቶብስ እና ዛሬ ደግሞ ወደ ስልክ መተግበሪያ ለማድረስ ተችሏል ብለዋል።

ይህም በዓለም ጥቂት ሀገራት የደረሱበትን ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ በማሳካት ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ በመሸጋገር የዳታ ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ የዳታ ማዕከል ግንባታን በአንድ ዓመት ለማጠናቀቅ በፍጥነት እየሠራች ትገኛለች።

ይህን ስኬት ይበልጥ በማጠናከር፣ ተሞክሮዎችን ለአፍሪካውያን ወንድሞች እና እህቶች በማካፈል የዓድዋን ድል በልማት በመድገም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ተምሳሌት ሀገር እንድትኾን የተጀመረውን ጉዞ ለማሳካት በቁርጠኝነት እንጓዝ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

#አሚኮ_ዜና #ቴክኖሎጂ_በመሶብ_አገልግሎት #ኢትዮጵያ 🇪🇹

ዘጋቢ: ኢብራሂም መሃመድ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“መንግሥት ለስፖርት ልማት ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው” ባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር
Next article🔐ከችግር ወደ መፍትሔ መሻገሪያ 🇪🇹የኢትዮጵያ ታላቁ የምክክር ጉባኤ !