
ባሕር ዳር: ሰኔ 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለማችን በአቬሽን ዘርፍ ፉክክሩ ከፍ እያለ መጥቷል። ሀገራት የአቬሽኑን ዘርፍ መገለጫቸው አድርገው በሰፊው ነው የሚሠሩበት። ከሚያስገኘው ጥቅም ባለፈ ሀገራትን በማስተዋወቅም ብሔራዊ ኩራት እና መተማመኛ ዘርፍ እየኾነ መጥቷል። በዚህ ዘርፍ ኢትዮጵያ ወደ ዓለም ሀገራት ዘልቆ ለመግባት እና ተወዳዳሪ ለመኾን መሥራት ከጀመረች ቆይታለች።
በቅርቡም በዓለማችን ከሚገኙ ግዙፍ አየር ማረፊያዎች ተራ የሚሰለፍ እና በአፍሪካም ቀዳሚውን የግዙፍነት ደረጃ የያዘ አየር ማረፊያ በቢሾፍቱ ተጀምሮ ግንባታው እየተቀላጠፈ ነው። በዚህም የአቬሽኑ ዘርፍ የሀገር ኩራት መኾኑን በተግባር አሳይቷል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዘመዴነህ ሙላቱ እንደሚሉት የኢትዮጵያ የአቪዬሽን ታሪክ በፈጠራ፣ በቁርጠኝነት እና በአፍሪካ ቀዳሚ የመኾን አሻራ የተሞላ ኩሩ ታሪክ ያለው ነው። ይህ ጉዞ ከ90 ዓመታት በፊት በአንዲት አነስተኛ አውሮፕላን ተጀምሮ፣ ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደሚገነባ ግዙፍ የኤርፖርት ሲቲ ሜጋ ፕሮጀክት ተሸጋግሯል።
ዛሬ አየር መንገዱ በዘመናዊ አውሮፕላኖች እንደ ኤርባሰ ኤ350 እና ቦይንግ 787 በመታገዝ ከ130 በላይ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን የሚያገናኝ የሀገሪቱ ኩራት እና የዲፕሎማሲ ምሰሶም ነው።
አሁን ያለው የቦሌ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ በዓመት እስከ 25 ሚሊዮን መንገደኞችን ለማስተናገድ የሚያስችል የማስፋፊያ ሥራ ቢሠራም በከተማ መሐል በመገኘቱ ምክንያት የበለጠ ለማስፋት ተጨማሪ ቦታ አጥቷል። በመኾኑም የቀጣይ 20 እና 30 ዓመታት የዕድገት ራዕይን ለማሳካት በቢሾፍቱ አካባቢ አዲስ ዘመናዊ አየር ማረፊያ መገንባት ግድ ኾኗል ብለዋል።
አየር ማረፊያው ቢሊዮን ዶላሮች ተበጅተውለት በ3 ዋና ዋና ምዕራፎች ተከፍሎ የሚገነባ ሲኾን ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅም በአፍሪካ ግዙፉ አየር ማረፊያ ይኾናል።
ሥራው ሲጠናቀቅም በዓመት እስከ 110 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል። 4 ትይዩ የኾኑ የአውሮፕላን ማኮብኮቢያዎችም ይኖሩታል።
ይህ ፕሮጀክት ተራ አየር ማረፊያ ሳይኾን ራሱን የቻለ “ኤርፖርት ሲቲ” ኾኖ ነው የሚገነባው የሚሉት ባለሙያው በውስጡም እጅግ ዘመናዊ የሆቴል እና የኮንፈረንስ ማዕከላት፣ የንግድ እና የገበያ ማዕከላት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና መሥሪያ ቤት እና የሠራተኞች መኖሪያ መንደሮች፣ የአውሮፕላን ጥገና እና የካርጎ ተርሚናሎችን ያካትታል።
አዲሱ አየር ማረፊያ ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር በፈጣን የባቡር ትራንስፖርት እና በዘመናዊ የፍጥነት መንገድ የሚገናኝ በመኾኑ መንገደኞች ያለምንም የትራፊክ መጨናነቅ በቀጥታ አዲስ አበባ መግባት እና መውጣት ይችላሉ።
ይህ ታሪካዊ ፕሮጀክት የኢትዮጵያን የቱሪዝም፣ የወጭ ንግድ እና የአቪዬሽን መሪነት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግረዋልም ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ነው።
#አሚኮ_ዜና #አቬሽን #ኢትዮጵያ 🇪🇹
በምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
