የኢትዮጵያ ምልክት፣ የአፍሪካ ኩራት‌!

5

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‌አፍሪካውያን በቅኝ ግዛት በነበሩበት፤ ቅኝ ገዢዎች ከአፍሪካ ምድር ባልወጡበት፣ ዓለም ለአፍሪካ ነጻነት ፊቱን ባዞረበት፣ ፍትሕ ለነጭ ብቻ ባዘነበለችበት በዚያ ዘመን የነጻነት ምልክቷን ስሎ በአፍሪካ ሰማይ ላይ ይመላለስ ነበር፡፡

በነጻነት ምልክቷ፣ በሉዓላዊነት አብነቷ በአረንጓዴ ቢጫ ቀዩዋ ሠንደቅ አጊጦ ለአፍሪካውያን ተስፋን ይሰጣቸው፣ ነጻነትን ያሳያቸው፣ በራስ መኩራትን ያስተምራቸው፣ በራስ መድመቅን ያስመለከታቸው ነበር፡፡ ሠንደቅ ዓላማዋ በቅኝ ግዛት ያልተያዘች፣ በነጻነት ያበራች፣ በክብር የተጠበቀች፣ በማንም በምንም ያልተደፈረች፣ ለዘመናት በኩራት እና በክብር የኖረች፣ ለአፍሪካ እና ለመላው የጥቁር ሕዝብ ሁሉ ተስፋ እንደኾነች ያሳያቸውም ነበር፡፡

ኢትዮጵያ በታሪክ እንደከበረች፣ በነጻነት እንደ ጀንበር እንዳበራች፣ በአፍሪካ ምድር ነጮችን ያንበረከከች፣ ከእግሯ ሥር የጣለች፣ የቅኝ ግዛትን መንፈስ የሰበረች፣ ድል አድራጊነትን ብቻ የታደለች እንደኾነች ለዓለም ያሳይ ነበር፡፡

አፍሪካን ያስተሳሰረ፣ የአፍሪካን ክብር እና ታሪክ ለዓለም የነገረ፣ አፍሪካን ከተቀረው ዓለም ጋር ያገናኘ፣ ዝናው ከዓለም እስከ ዓለም የናኘ ነው የኢትየጵያ አየር መንገድ፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአየር መንገድ ባሻገር ነው፣ ስለ ምንቢሉ ፓን አፍሪካኒዝም ተቀንቅኖበታል፣ የአፍሪካ አንድነት ጠንክሮበታል፣ አፍሪካውያን ተሠባሥበውበታል፣ ክብራቸውን እና ታሪካቸውን ለዓለም ነግረውበታል፣ የራሳቸው የኾነ ውብ ማንነት እንዳላቸው ተናግረውበታልና።

ይህ አየር መንገድ የአፍሪካን ዲፕሎማሲ አስፍቷል፤ የአፍሪካን ውብ ጸጋ አሳይቷል፤ አፍሪካን ለማየት የናፈቁ ከመላው ዓለም የሚገኙ ሰዎችን ወደ አፍሪካ አምጥቷል፡፡ ማንነት እየተገለጠበት፣ ዘመን እየተዋጀበት፣ ክብር እና ታሪክ እየተነገረበት ዓመታትን ተሻግሯል፡፡

ለኢትዮጵያ ምልክት፣ ለአፍሪካም ኩራት የኾነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካውያን እንኳን በራሳቸው የሚኮሩበት ሀብት ይቅርና በራሳቸው የሚያዝዙበት ማንነት ባልነበራቸው ዘመን የተመሰረተ ታላቅነት እና አፍሪካዊነት የሚገለጽበት የኩራት እና የክብር ምንጭ ነው፡፡ የኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ሀብትም ነው፡፡

ሰላማዊት ገብረ እግዚአብሔር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለምን ስኬታማ ኾነ? ለሌሎች የሕዝብ ኩባንያዎችስ ምን አይነት ትምህርት ይሰጣል? በሚል ርእስ ባጠኑት ጥናት በኢትዮጵያ የአየር ትራንስፖርት ረጅም ታሪክ አለው፤ ኢትዮጵያ የአየር ትራንስፖርት ቴክኖሎጂ ከተጀመረ ከሁለት አሥርት ዓመታት በኃላ ነው የጀመረች፤ የኢትዮጵያ አቬሽን ታሪክ የሚጀምረው በ1921 ዓ.ም ነበር ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሀገሪቱን የትራንስፖርት ችግሮች በመፍታት ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ ማዕከላዊ መንግሥቱ ከክፍለ ሀገራቱ ጋር ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር በማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በፈረስ፣ በበቅሎ እና በሌሎች የየብስ ትራስፖርት ሲደረጉ የነበሩ አድካሚ እና ረጅም ጊዜ የሚወስዱ ጉዞዎችን በማሳጠር ግንኙነት እንዲፋጠን እና እንዲዳብር አድርጓል ይላሉ፡፡

ትራንስፖርት ከሀገር ልማት እና ከሕዝቦቿ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ደኅንነት ጋር በማይነጣጠል መልኩ የተቆራኘ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከሌላው ዓለም ጋር ያላት ግንኙነት የተጠናከረ እና ዓለማቀፋዊነት እንዲጎለብት አድርጓል ነው የሚሉት፡፡ ወደብ ለሌላት ሀገር የንግድ ግንኙነቷ እንዲሳለጥ፣ የቱሪዝም እንቅስቃሴዋ እንዲያድግ ያደረገ አንጋፋ ተቋም ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ችግሮችን እየተቋቋመ ትርፋማ እና ውጤታማ የኾነ ተቋም መኾኑንም አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ መስፍን ጣሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካውያንን እርስ በእርስ የማስተሳሰር እና ከሌላው ዓለም ጋር የማገናኘት ሥራ እየሠራ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካውያንን በማገናኘቱ ኩራት ይሰማዋል፤ አፍሪካውያንን ለዓመታት በማስተሳሰሩ ደስታ ይሰጠዋል ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ መዳረሻውን እያሰፋ፣ በመዳረሻዎቹ ደግሞ የበረራ ድግግሞሽን እያሳደገ የመጣ አንጋፋ ተቋም ነው ይላሉ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካውያንን ምጣኔ ሀብት እና ማኅበራዊ ግንኙነት አሳድጓል፣ አየር መንገዱም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል ነው የሚሉት፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለአፍሪካ ሀገራት አየር መንገዶችም አርዓያ እና ትምህርት ቤት ኾኗል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን የማስተሳሰሩን፣ የአፍሪካ ኩራት መኾኑን አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡ አፍሪካ ውስጥ ጠንካራ የኾነ አቬሽን እንዲኖር እንደሚሠራም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለዘመናት የገነባው ወርቃማ የሥራ ባሕል አለው፤ ኢትዮጵያውያን አየር መንገዱን የመስተንግዶ እና የእንክብካቤ መለኪያ አድርገው እስኪቆጥሩት የደረሰ የመስተንግዶ ልምድ አለው፡፡ ይህ አየር መንገድ አሁን ደግሞ ከነበረበት አቅም የበለጠ የሚያልቀውን፣ የአፍሪካ አርዓያ እና ኩራትነቱን የሚያስቀጥለውን ሥራ ጀምሯል፡፡

ኢትዮጵያን ከዚያም ባሻገር አፍሪካን የአየር ትራንስፖርት ማዕከል የሚያደርጋትን የቢሾፍቱን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ጀምራለች፡፡ ይህ ፕሮጄክት የአፍሪካ ግዙፉ ነው፣ ለአፍሪካም ተስፋ እና በረከት ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታን ባሰጀመሩበት ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጥንታዊት ሀገር ምልክት፣ የጥንታዊት ሀገር ኩራት፣ የጥንታዊት ሀገር መሻት፣ ማሳያ ኾኖ ቆይቷል ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፉት ዓመታት አልጋ በአልጋ የኾነ ጉዞ አላሳለፈም፤ የመንግሥታትን መውደቅ እና መነሳት ተሸክሞ ዕድገቱን ሳያቋርጥ ማለፍ ችሏል ነው ያሉት፡፡
ተፈጥሯዊ ችግሮች፣ ጦርነቶች ዕድገቱን ሳይገቱት ቆይተዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፈር ቀዳጅ ነው፤ የአፍሪካ ሀገራት ነጻ ሳይወጡ በአፍሪካ ግንባር ቀደም ተቋም የኾነ ትልቅ ተቋም ነው ይላሉ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የስኬቱ ሚስጥር የኮርፖሬት ባሕል በመገንባቱ ነው የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለደኅንነት ቅድሚያ የሚሰጥ ነው፤ ሰላማዊ እና ደኅንነቱ የተረጋገጠ አየር መንገድ ነው፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ተሸክሞ ኢትዮጵያን የሚያሳይ ነው ይሉታል።

የኢትዮጵያ ልክ መበልጸግ ነው፤ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚውን ምጣኔ ሀብት ትገነባለች፤ ለአፍሪካ ነጻነት ታጋይ እንደነበረች ዳግም ታስመሰክራለች ነው ያሉት፡፡

#አሚኮ_ዜና #አቬሽን #ኢትዮጵያ

በታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያ የተከለችው ድንቅ አፍሪካዊ ስም እና የምጣኔ ሃብት መሰረት