🕊️እገታ፣ ዘረፋ እና ግድያ ይብቃ! 🚌 🛞

27

 

የሰው ልጅ በሕይወት ለመኖር የደም ዝውውር እንደሚያስፈልገው ኹሉ ለአንድ ሀገር ኹለንተናዊ እድገት እና ሕልውናም ትራንስፖርት የደም ሥር ነው።

ትራንስፖርት የማይነካው ዘርፍ የለም። ዜጎች ወደ ሕክምና ተቋማት ቢሄዱ፤ የግብርና እና የፋብሪካ ምርቶች ወደ ገበያ ማዕከላት ቢደርሱ፤ የሕክምናና የምግብ እርዳታዎች ለተጎጂዎች ቢቀርቡ፤ የሕዝብን ደኅንነት እና የሕግ ማስከበር ሥራዎች ቢከናወኑ በጥቅሉ የኹሉም የመንግሥት እና የሕዝብ የዕለት ከለት ተግባራት የሚሳለጡት በዚሁ በትራንስፖርት ነው።

የትራንስፖርት ደኅንነት በተናጋ ቁጥር ደግሞ የሀገር ልማት፣ የሕዝብ ሰላም እና የኢኮኖሚ ዕድገት አብሮ ይደናቀፋል።ፕሮፌሰር ፒተር ኒውማን የተባሉ ምሁር “የትራንስፖርት መስተጓጎል የካፒታል ዝውውር ፍጥነትን የሚገታ እና የከተሞችን እንቅስቃሴ የሚያጓትት የኢኮኖሚ በሽታ ነው” ብለውታል።

ሰላም የሚፈልገው ይህ ዘርፍ ባለፉት ዓመታት በግጭቶች የተነሳ መስተጓጎል ገጥሞታል።

በተለይ ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ በሚወስዱ ጎዳናዎች እገታ፣ ዘረፋ እና ግድያዎች ከተባባሱ ዓመታት ተቆጥረዋል። በዚህ የተነሳ በቀጣናው የየብስ ትራንስፖርት በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱ ይነገራል።

በአማራ ክልል የአማራ ሕዝብ አዲስ አበባ መግባት ተከለከለ እና ሌሎች በደሎች ደረሱበት በሚል ጫካ የገቡ ታጣቂዎች በሚፈጥሯቸው ግጭቶች፤ በሚፈጽሙት የመንገድ ላይ እገታ፤ ዘረፋ እና ግድያ ማኅበረሰቡ እንደልቡ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ካቆመ ዓመታት ተቆጥረዋል።

ይህም ነዋሪዎችን በሌለ ጎናቸው የአየር ትራንስፖርትን በአማራጭነት እንዲጠቀሙ አስገድዷቸዋል። የአየር ትራንስፖርት በሌለባቸው አካባቢዎች እና አውሮፕላን መጠቀም የማይችሉ በርካታ ነዋሪዎች በየብስ ትራንስፖርት ለታጣቂዎች ሰለባ ኾነዋል።

በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱት ጽንፈኛ ታጣቂዎች ከመዝረፍ፣ ከማገት እና ከመግደል ባለፈ የትራንስፖርት እገዳ በመጣል አዲስ አበባ መግባት ተከለከለ ያሉትን ሕዝብ በቀዬው የመንቀሳቀስ ነጻነቱን ገፍፈውታል። በከፍተኛ ወጭ የአየር ትራንስፖርት እንዲጠቀም በማድረግ ለድህነት ዳርገውታል።

ታጣቂዎቹ ባለፉት አራት ዓመታት በርካቶችን አግተው በሚሊዮን ብር በማስከፈል በርካታ ነዋሪዎች ያፈሩትን ጥሪት ሽጠው እንዲከፍሉ በማድረግ ብዙዎችን ለድህነት ዳርገዋል። እናት “ልጄ ታግቶብኝ” ብላ ለልመና አደባባይ የወጣችውም በእነሱ ምክንያት ነው። የተጠየቁትን ገንዘብ መክፈል ባለመቻላቸው በአሰቃቂ ሁኔታ በጥይት እሩምታ የተገደሉትንም ሀገር ይቁጠራቸው።

በሚያካሂዱት የትራንስፖርት ገደብ እናት ሆስፒታል ሳትደርስ ሕይወቷ እንዲያልፍ፤ የሕክምና ክትትል ያላቸው ነዋሪዎች ሕክምና አጥተው እንዲሞቱ፤ የአርሶ አደሮችን ግብዓት በመዝረፍ ምርታማነታቸው እንዲቀንስ እና ሌሎችንም በደሎች በአማራ ሕዝብ ላይ መፈጸማቸው የአደባባይ ሐቅ ነው።

በዚህ አስከፊ ሂደት አሽከርካሪዎችም ከፍተኛ ዋጋ ከፍለዋል። በርካቶች ላባቸውን ጠብ አድርገው ያፈሩትን ንብረት አጥተዋል። በታጣቂዎች የተገደሉትም በርካታ ናቸው። የተፈጸመው ግፍ ብዙ ነው።

ይህ ሁሉ በአማራ ሕዝብ ላይ የተፈጸመው በደል ለሕዝብ ተነሳን ብለው ጫካ በገቡ ጽንፈኛ ቡድኖች ነው። ይህንንም ከነዋሪዎች ባለፈ ታጣቂዎች ራሳቸው በተደጋጋሚ አረጋግጠዋል።

ግጭት የአማራ ሕዝብን ማኅበራዊ እረፍት ነስቶታል። ሰላም የመላው የአማራ ሕዝብ ብሎም የኢትዮጵያውያን መሠረታዊ ፍላጎት ከኾነ ውሎ አድሯል። ሰላምም የቀን ተቀን ጥሪው ኾኗል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በደብረ ማርቆስ ከተማ የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት አውሮፕላን ማረፊያን መርቀው ሥራ ሲያስጀምሩ በረራ መጀመሩ መልካም ነገር መኾኑን አንስተዋል። ለአውሮፕላን መክፈል የማይችሉ ወይም የማይፈልጉ በየብስ ትራንስፖርት ከማርቆስ ባሕር ዳር ወይም ከማርቆስ አዲስ አበባ መሄድ እንዲቻላቸው ሰላም በእጅጉ አስፈላጊ መኾኑን መናገራቸው ይታወሳል።

መንግሥታቸውም ውይይት እና ንግግር ለሚፈልጉ ለማንኛውም ሰዎች በሩ ክፍት መኾኑን በድጋሜ አረጋግጠው እንቀራረብ፣ እንወያይ ሀገራችን ሰላም እናድርግ በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ መላው የአማራ ሕዝብ የሚጋራው እና የሚፈልገው ነው። የአውሮፕላን ጉዞ የኢኮኖሚ አቅማቸው ለሚፈቅድላቸው እንጅ ለኹሉም የኅብረተሰብ ክፍል አይኾንም። እናት በሐኪም ቤት እንድትወልድ፤ የታመመ እንዲታከም፤ አርሶ አደር እንዲያመርት፤ ልጆች እንዲማሩ፤ መሠረተ ልማት እንዲስፋፋ ሰላም በእጅጉ ያስፈልጋል።

የኹሉም ኢትዮጵያውያን የልብ መሻትም ሰላም ሰፍኖ ኹሉም ከቦታ ቦታ በነጻነት የሚንቀሳቀስበት ጊዜ እንዲመጣ ነው። የግጭት አዙሪት፣ እገታ፣ ዘረፋ እና ግድያ ይብቃ። በመላው ኢትዮጵያ ሰላም ይስፈን 🕊️🇪🇹🙏

#AMICO #PeaceForEthiopia #FreeTransportation 🛣️ 🚌

#ባሕር_ዳር፡ሐምሌ13/2018 ዓ.ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየመረጃ ምሥጠራ ምን ጥቅም እና ጉዳት አለው?
Next article🌍 ለእኛ የመጀመሪያ፤ የዓለም ሀገራትን ከቀውስ ያወጣ የሰላም ጋሻ – ሀገራዊ ምክክር 🕊️