
ባሕር ዳር: ሰኔ 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በቢሾፍቱ የሚገነባው አዲሱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የሀገሪቱን የአቪዬሽን ታሪክ ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ሜጋ ፕሮጀክት ነው። ለኢትዮጵያ በርካታ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ስትራቴጂካዊ ጥቅሞችን ይዞም ይመጣል።
አየር መንገዱ የአፍሪካ ቀዳሚ የአቪዬሽን መናኸሪያ ለመኾን የያዘውን ራዕይ ዕውን ለማድረግ ያለመ ነው።
የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪው የኢትዮጵያን ከፍታ የሚያስቀጥል ከዓለም አቀፉ የንግድ እና የኢኮኖሚ ሰንሰለት ጋር ይበልጥ የሚያስተሳስር ታሪካዊ እና ስትራቴጂካዊ የልማት ምሰሶም ነው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ መስፍን ጣሰው በተለያየ ወቅት ለሚዲያዎች በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት አየር መንገዱ በፍጥነት እያደገ እና የማያቋርጥ የማሥፋፊያ ሥራዎችን እያከናወነ ዘልቋል።
በቀጣዮቹ ዓመታት በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሊያጋጥም የሚችለውን መጨናነቅ ቀድሞ በማጥናት አዲስ የአውሮፕላን ማረፊያ በቢሾፍቱ መገንባት አስፈላጊ ኾኖ መገኘቱን አብራርተዋል።
ዋና ሥራ አሥፈጻሚው እንደገለጹት የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ በሁለት ምዕራፎች የሚገነባም ነው።
ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት የአፍሪካን የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ አስሮ የያዘውን የመሠረተ ልማት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ትልቅ ተስፋ ተጥሎበታል።
ለአፍሪካም ትልቅ አርዓያ ይኾናል ነው ያሉት።
በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣናን ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፤ የኢትዮጵያን የወጭ ንግድ (ኤክስፖርት) ያፋጥናል።
ለአዳዲስ የሆቴሎች መስፋፋት በር ይከፍታል፤ የቱሪስት ፍሰቱን ያቀላጥፋል። ለበርካታ ዜጎችም የሥራ ዕድል ይፈጥራል። የትራንስፖርት እና የንግድ መነቃቃትንም ያመጣል።
በተጨማሪም ሁለት ተርሚናሎች በሁለተኛው ምዕራፍ የሚገነቡ ናቸው።
የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ አራት ተርሚናሎችም ይኖሩታል። የአውሮፕላን ማረፊያው በዓለም ላይም እጅግ ዘመናዊ ከኾኑት ተርታ የሚመደብ ነው ብለዋል።

ሙሉ በሙሉ ሲጠናቅ በዓመት እስከ 110 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም እንደሚኖረው ተገልጿል። ይህም በአፍሪካ ቀዳሚው የአውሮፕላን ማረፊያ ያደርገዋል።
ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
