አረንጓዴ አሻራ ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ አርዓያ እንድትኾን አድርጓታል።

4
ባሕር ዳር: ሰኔ 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ተግባር ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለምግብ ዋስትና እና ለሀገር ገጽታ ግንባታ ትልቅ ምዕራፍ የከፈተ ሀገራዊ ንቅናቄ ነው።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት መረጃ የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ከተጀመረበት 2011ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያውያን ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ተክለዋል። ይህም በሀገሪቱ ለበርካታ አስር ዓመታት የተራቆቱ መሬቶች እንዲያገግሙ እና የሀገሪቱ የደን ሽፋን ከ17 በመቶ ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ገደማ እንዲያድግ አድርጓል።
የተተከሉት ዛፎችም የአፈር መሸርሸርን በመከላከል የከርሰ ምድር ውኃ እንዲጠናከር፣ የውኃ ምንጮች እና ወንዞች እንደገና ወደነበሩበት እንዲመለሱ ረድተዋል። የካርቦን ልቀትን በመቀነስ ረገድም ሀገራዊ እና ዓለምአቀፋዊ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
ለኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እና ለምግብ ዋስትናም አስተዋጽኦ አድርጓል። ከተራ ዛፎች በተጨማሪ ለምግብነት የሚውሉ እንደ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ፓፓያ እና ቡና ያሉ ዘላቂ ጠቀሜታ ያላቸው ተክሎች በስፋት መተከላቸው አርሶአደሮች ከምግብ ፍጆታ ባሻገር ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ አድርጓል።
ኢትዮጵያ አቦካዶ ምርትን ለውጭ ገበያ በመላክ በአፍሪካ ደረጃ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ እንድትልም አድርጓል። የቡና ልማት መስፋፋት እና የውጭ ምንዛሬ ግኝትም ማደግ ችሏል።
በችግኝ ማፍላት፣ በመንከባከብ እና የጥበቃ ሥራዎች ላይ ተሳትፎ ላደረጉ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድሎችን ፈጥሯል።
ኢትዮጵያውያን ሃይማኖት፣ ብሔር፣ ዕድሜ እና መሠል ጉዳይ ሳይገድባቸው ለአንድ ዓላማ በጋራ እንዲሰለፍ በማድረግ ረገድ ትልቅ ማኅበራዊ ትስስር ፈጥሯል። ችግኝ መትከል ብቻ ሳይኾን የመንከባከብ እና የማሳደግ “የአረንጓዴነት” ባሕል እና ንቃተ ህሊና እንዲዳብርም አድርጓል።
ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ የምታደርገውን ጥረት ለዓለም በማሳየት ረገድም የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ኾኗል።
በአጭር ጊዜ ውስጥ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ አርዓያ መኾን እንድትችል አድርጓል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የዓለም ምግብ እና እርሻ አግሪኮል ሸልማትን፣ ልዩ የአፍሪካ አመራር ሽልማትን ማግኘታቸው፣ ኢትዮጵያ 2ኛውን የአፍሪካ የአየር ንበረት ጉባኤ ተመርጣ ማስተናገዷም ሌሎች ማሳያዎች ናቸው።
ኢትዮጵያ 2ኛውን የተባበሩት መንግሥታት የሥርዓተ ምግብ ጉባኤ ማስተናገዷ፣ በ8ዐኛው የዓለም ምግብ እና እርሻ ድርጅት ጉባኤ ለዘላቂ ደን ልማት የተሰጣት ዕውቅና እና ኢትዮጵያ ኮፕ-32ን ለማስተናገድ መታጨቷም ሌላው የስኬት ማሳያ ነው።
የአረንጓዴ አሻራ የአረንጓዴ መልክአምድር ብቻ ሳይኾን ለቀጣዩ ትውልድ የሚተርፍ የተፈጥሮ ሀብት፣ የተረጋገጠ ምግብ እና የተስተካከለ የአየር ንብረት ማስረከቢያ ታሪካዊ አሻራም ነው።
የሕዝብ ባለቤትነትን አጠናክሮ ማስቀጠል (አረንጓዴ ባሕል መገንባት)፤ አማራጭ የኀይል አቅርቦት ሥራዎችን ማስፋት እና በደን ላይ የሚደርሰውን ጫና መቀነስ፤ የሕግ እና የፖሊሲ ማሻሻያ የሚፈልጉ ጉዳዮችን በጥናት ለይቶ መመለስ ደግሞ የቀጣይ የሀገሪቱ የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው።
ከአረንጓዴ አሻራ የሚገኘውን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በማጠናከር የባለድርሻ አካላት እና የተቋማት ቅንጅታዊ አሠራርን ማጠናከር፤ በክረምት ወራት የሚተከሉ ችግኞችን በበጋ ወራት መንከባከብም ሌሎች የትኩረት አቅጣጫዎች እንደኾኑም ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“በሀረሪ ክልል በማዕድን ዘርፍ ላይ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል” ርእሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ
Next articleየኢትዮጵያን ከፍታ የሚሳየው የቢሾፍቱ ዓለም ዓቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ