
ባሕር ዳር: ሰኔ 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እያደረገችው ባለው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በአማራ ክልል ከፍተኛ ውጤት እየተመዘገበ መኾኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል።
በቢሮው የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃ እና አጠቃቀም ዳይሬክተር አስመለዓለም ምህረቱ እንደገለጹት ላለፉት ዓመታት በተከናወኑ ተከታታይ ሥራዎች የተራቆቱ መሬቶች በማገገማቸው የክልሉ የደን ሽፋን ከነበረበት 13 ነጥብ 9 በመቶ ወደ 18 ነጥብ 9 በመቶ ከፍ ብሏል።
በዘንድሮው መርሐ ግብርም ከ261ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት ተጠናቅቋል። የችግኞችን ዕድገት በቀላሉ ለመከታተል የሚያስችሉ አሠራሮችም ተዘርግተዋል።
አሁን ላይ ችግኙ የሚተከልበት ቦታ፣ የሚተክለው እና እንክብካቤ የሚያደርገው አካል አስቀድሞ በስምምነት ስለሚለይ የመጽደቅ ዕድሉ በከፍተኛ ደረጃ አድጓል። በተለይም አርሶ አደሮች ጥቅሙን በመረዳት በራሳቸው ጓሮ እና ማሳ ላይ የፍራፍሬ ችግኞችን ማፍላት እና መትከል መጀመራቸው አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል ነው ያሉት። ይህም አረንጎዴነትን በማጎናጸፍ የምድርን ጤና ከመጠበቅ አልፎ የምግብ ሉዓላዊነትን የሚያረጋግጥ የኢኮኖሚ ዘብ መኾን ችሏል።
ለቀጣይ ስኬታማነት እንደ ዓባይ፣ አዋሽ፣ ተከዜ እና ደናክል ያሉ አራቱን ዋና ዋና ተፋሰሶች መሠረት ያደረጉ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ በተለይም በተራራማ እና በተራቆቱ ቦታዎች ላይ ልዩ ትኩረት መስጠት ዓመቱን ሙሉ የሚፈሱ የውኃ ምንጮችን ለማግኘት ወሳኝ መኾኑን አብራርተዋል።
የአረንጓዴ አሻራ ሥራ የምግብ፣ የቤት መስሪያ እንጨት እና የእንስሳት መኖ ምንጭ በመኾኑ የህልውና ጉዳይ ነው ያሉት አቶ እስመለዓለም አርሶ አደሮች የመንከባከብ፣ ባለሙያው በሳይንሳዊ መንገድ የመምራት፣ መሪዎች የመከታተል እና የመደገፍ ኀላፊነታቸውን በቅንጅት ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
