ታላቁ የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ኘሮጀክት የኢትዮጵያ የመቻል ማሳያ ነው።

8
ባሕር ዳር: ሰኔ 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ታሪክ በግዙፍ በጀት እና በሥራ መጠኑ በዓይነቱ ለየት ያለ ሜጋ ፕሮጀክት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ያስጀመሩት ይህ ታላቅ መሠረተ-ልማት ሀገሪቱን በቀዳሚ የአቪዬሽን ማዕከላት ተርታ ለማሰለፍ በከፍተኛ ትጋት እየተከናወነ የሚገኝ ኘሮጀክት ነው።
​ፕሮጀክቱ ከአዲስ አበባ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እየተገነባ ይገኛል። ሲጠናቀቅ በዓመት እስከ 110 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል።
በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 12 ቢሊዮን ዶላር የተመደበለት ፕሮጀክት በአፍሪካ ደረጃም ትልቁ የአቪዬሽን መሠረተ ልማት ነው። ፕሮጀክቱ ያለማቋረጥ በሳምንት ሰባት ቀን እና 24 ሰዓት እየተገነባ ነው።
በአሁኑ ወቅት ከ8ሺህ በላይ ዜጎች በቀጥታ በሥራ ላይ ተሠማርተዋል ። እስከ 4ሺህ የሚደርሱ የተለያዩ ማሽኖች የግንባታውን ሂደት እያፋጠኑት ይገኛሉ።
ይህ ፕሮጀክት ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ አህጉር የንግድ እና የኢኮኖሚ ትስስር ትልቅ ፋይዳ አለው። በተለይም የአፍሪካ ነፃ አህጉራዊ የንግድ ቀጣናን ውጤታማ ለማድረግ ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድን ዓለም አቀፍ የበረራ አቅም በማሳደግ፣ የአቪዬሽን የበላይነትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው።
​ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የግንባታ ሂደቱን በጎበኙበት ወቅት እንደገለጹት እንዲህ ያለው የሰው ኀይል እና የማሽን እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ያልነበረ አዲስ ልምድ ነው።
ኘሮጀክቱ ሀገሪቱን ከፍ አድርጎ የሚያጎላ፣ አፍሪካን የሚያነቃቃ ግዙፍ ኘሮጀክት እንደኾነም ጠቁመዋል። ይህ ኘሮጀክት “አፍሪካ ማቀድ እና መሥራት እንደምትችል ለዓለም የምናሳይበት ነውም” ብለዋል።
የአትዮጰያ የመቻል ማሳያ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የኢትዮጵያን አጠቃላይ የኢኮኖሚ ገጽታ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀይር ነው የገለጹት። ይህ ትልቅ ሜጋ ኘሮጀክት ኢትዮጵያን ለዓለም ገልጦ ያሳየ ነውም ብለዋል።
በሀገራዊ ምርት ውስጥ ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረውም ገልጸዋል። እየተገነባ የሚገኘው ይህ ሜጋ ኘሮጀክት በታቀደለት ጊዜ ይጠናቀቃል ተብሎም ይጠበቃል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበጎንደር ከተማ እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎች ለከተማዋ ውበትን የጨመሩ ናቸው።