ከገናና የሰማይ ላይ ስም እስከ ቅንጡ የምድር ላይ ክብር!

11
አዲስ አበባ: ሰኔ 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ አቪዬሽን ታሪክ በዓለም አቀፍ መድረክ አዲስ ምዕራፍ እየከፈተ ነው። ገናና ክብሩን ጠብቆ እና የታላቅ ሀገር ስም እና ቀለም ተሸክሞ ከሰማይ ሰማይ የነገሠው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በስሙ ልክ የኾነ ግዙፍ አውሮፕላን ማረፊያ እየተገነባለት ነው።
ይህ ታላቅ ፕሮጀክት የሰፈረበት የቢሾፍቱ መሬት ዛሬ ለኢትዮጵያዊ ሁሉ ኩራት ነው። ለምሥራቅ አፍሪካ አቪዬሽን ማዕከልነት የተመረጠ እና አየር መንገዱ የሰማይ ገናናነቱን የጠበቀ ስሙን በምድር ላይም የሚተክልበትም ነው።
አየር ማረፊያው አሁን ባለው የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ የሚፈጠረውን የትራፊክ መጨናነቅ ለመቀነስ ወሳኝ ነው። በሰማይ ላይ ስሙ እንደናኘው ሁሉ፣ በምድር ላይም ከዘመን ልቆ የዘመነ፣ በሀገር ክብር ልክ የሰፋ እና ለደንበኞቹ የተመቸ መሠረተ ልማት በቢሾፍቱ እየተከለ ነው።
በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ወቅት የተበሰረው ይህ ግዙፍ አውሮፕላን ማረፊያ፣ ተራ ግንባታ ሳይኾን የቴክኖሎጂ እና የሥልጣኔ ውጤቶች የወለዱት፣ እጅግ የረቀቀ እና ዓለም ሁሉ ዐይኑን የጣለበት የሀገር ስም ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ፕሮጀክቱን በጎበኙ ጊዜ እንደተናገሩት ፕሮጀክቱ ጥራት፣ ውበት እና ፍጥነትን ባጣመረ የፕሮጀክት አሥተዳደር እየተከናወነ ነው። ሲጠናቀቅም በዓመት በሚሊዮን የሚቆጠሩ መንገደኞችን በማስተናገድ በቱሪዝም ዘርፍ፣ በሎጂስቲክስ እና በንግድ እንቅስቃሴዎች ኢትዮጵያን ከስመ ጥር ሀገራት ተራ የሚያሰልፍ ይኾናል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሀገርም አልፎ የአፍሪካ የኩራት መገለጫ ኾኖ እንደኖረው ሁሉ በቢሾፍቱ የሚተከለው ይህ ግዙፍ መሠረተ ልማትም የኢትዮጵያን ብርታት እና የዕድገት ፍላጎት የሚያሳይ ነው።
ኢትዮጵያ በስመ ጥር አውሮፕላኖቿ የዓለምን ሰማይ በተቆጣጠረችበት ልክ በምድር ላይም በቢሾፍቱ መሬት ስሟን በወርቃማ ፊደላት እየጻፈች ነው።
ይህ አውሮፕላን ማረፊያ የኢትዮጵያን የአቪዬሽን ዘርፍ ወደ ሌላ ከፍታ የሚያሸጋግር ብቻ ሳይኾን ለቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፍ የዕድገት አሻራ ነው። ቢሾፍቱ ዛሬ በሰማይ ላይ ሥሙ ልቆ ሲነሳ ዓመታትን የዘለቀው አየር መንገዳችን ምድራዊ መኖሪያ፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር እና የኢትዮጵያውያን የጋራ ተስፋ መጋሪያም ኾናለች።
በአሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleእንደ ሀገር የሥነ ምግብ ሥርዓቶች እንዲስተካከሉ እየተሠራ ነው።
Next articleበጎንደር ከተማ እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎች ለከተማዋ ውበትን የጨመሩ ናቸው።