
አዲስ አበባ: ሰኔ 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ምግብ እና ሥነ ምግብ ማኅበር “እየተለዋወጡ ባሉ ተግዳሮቶች ውስጥ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያላቸውን የምግብ እና ሥነ ምግብ ውጤቶች ለማስመዝገብ የሥርዓት አቅምን ማጠናከር” በሚል መሪ መልዕክት 20ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን እያከበረ ይገኛል።
ባለፉት 20 ዓመታት ማኅበሩ በሥነ ምግብ ተሟጋችነት፣ ጨውን በአዮዲን ማበልጸግ ፕሮግራም ድጋፍ፣ በምግብ ደኅንነት አቅም ግንባታ እና በምርምር ውጤቶች ሥርጭት እና ትንተና ላይ በመሳተፍ ለሀገራዊ የሥነ-ምግብ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን ዶክተር ማስረሻ ገልጸዋል፡፡
ማኅበሩ በኢትዮጵያ ሁሉንም ዓይነት የተመጣጠነ ምግብ እጥረቶችን ለማስወገድ የሚደረገውን ጉዞ ለማፋጠን ማስረጃዎችን የማመንጨት፣ የባለሙያዎችን አቅም የማጠናከር እና የፖሊሲ ውይይቶችን ማካሄድ አሁንም በቁርጠኝነት አጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል፡፡
ማኅበሩ የ2019 ዓ.ም ዓመታዊ ጉባኤውን ለማስተናገድ በዝግጅት ላይ እንዳለም ገልጿል። ይህ ጉባኤ የምግብ ዋስትናን፣ ሥነ ምግብን እና ዘላቂ የልማት ውጤቶችን ለማሻሻል የሚደረጉ ሀገራዊ ጥረቶችን የሚደግፉ ወደ ተግባር ሊለወጡ የሚችሉ ምክረ ሀሳቦችን ያመነጫል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በዝግጅቱ ላይ የቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የአዳም ፋውንዴሽን መሥራችና ሊቀመንበር ደመቀ መኮንን፣ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ድጉማን ጨምሮ ሌሎች የተለያዩ የፌዴራል ተቋማት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ:-ድልነሳ መንግሥቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
