🕊 ልማት በማፋጠን ሰላምን ለማጽናት በትኩረት ይሠራል።

23

 

ባሕርዳር: ሰኔ 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ከልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በሰላም እና በልማት ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርጓል።

ውይይቱ ከምርጫ ማግሥት መንግሥት ሥራውን እንዲያስቀጥል፣ የምርጫ ውጤት የሕዝብ ቅቡልነት እንዲኖረው ለማስቻል ያለመ መኾኑ በውይይቱ ተነስቷል።

የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የኢትዮጵያ የስኬት ጎዳና እንዳይረጋገጥ፣ ኢትዮጵያውያን በአንድነት እንዳይቆሙ፣ ሕዝብ በድምጹ ሀገረ መንግሥት እንዳይመሠርት እና ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ እንዳይካሄድ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ሢሠሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

የታሪካዊ ጠላቶችን ሴራ በማክሸፍ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ኢትዮጵያ አሸንፋለች ነው ያሉት።

መንግሥት የከተማዋን ነዋሪዎች የመሠረተ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት መሥራቱንም ተናግረዋል። የከተማዋን ልማት በማፋጠን ሰላምን ለማጽናት በትኩረት ይሠራልም ብለዋል። የተጀመሩ መሠረተ ልማቶች እንዲጠናቀቁ በትኩረት እንደሚሠራም ጠቁመዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ምርጫው ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ኾኖ መጠናቀቁ እንዳስደሰታቸውም ገልጸዋል።

በቀጣይ የሚዋቀረው መንግሥት የተጀመሩ መሠረተ ልማቶችን በማጠናከር፣ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን በመፍታት፣ የኑሮ ውድነትን በማቃለል፣ ጠንካራ የሰላም ማስከበር ተግባራት በማከናወን ለሀገር ዕድገት መሥራት እንዳለበትም ተናግረዋል።

በባሕርዳር የተጀመሩ የኮሪደር እና ሌሎች መሠረተ ልማቶች የከተማዋን ገጽታ የቀየሩ፣ ጎብኝዎችን የሳቡ፣ ለወጣቶች የሥራ ዕድል የፈጠሩ፣ ለነዋሪው ምቹ ከባቢን የገነቡ ናቸው ብለዋል።

ያለ ሰላም ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የለም ያሉት ነዋሪዎቹ ሰላምን ለማጽናት የድርሻቸውን እንደሚወጡ አንስተዋል። ከተማዋ ወደ ቀደመ ሰላሟ መመለሷንም ተናግረዋል።

ኅብረተሰቡ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን በመደገፍ በባለቤትነት የመሠረተ ልማት ደኅንነትን መጠበቅ አለበትም ነው ያሉት።

#አሚኮ_ዜና #ሕዝባዊ_ውይይት #ባሕርዳር #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ 🇪🇹

ዘጋቢ:-ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article🕊️በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በሺህዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን ተቀብለዋል።
Next articleእንደ ሀገር የሥነ ምግብ ሥርዓቶች እንዲስተካከሉ እየተሠራ ነው።