🏢የጎንደር ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ግንባታ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ይጠናቀቃል።

33

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን የዜጎችን እንግልት ለማስቀረት ታስቦ ተግባራዊ የተደረገ ነው።

🏙️ለዚሁ አገልግሎት የሚኾኑ ዘመናዊ እና ምቹ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላትም በየከተሞቹ እየተገነቡ ወደ ሥራ ገብተዋል። አሁን ላይ በአማራ ክልል ከተሞች የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት ግንባታቸው እየተከናወነ ነው።

በሂደት ላይ ካሉት መካከልም የጎንደር ከተማ አሥተዳደር የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት አንዱ ነው።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት መምሪያ ኀላፊ ነጻነት መንግሥቴ ለአሚኮ እንደገለጹት በከተማው እየተገነባ የሚገኘው የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ሕንጻ በመጠናቀቅ ላይ ነው።

🏗️የግንባታ ሂደቱ በፍጥነት እና በጥራት እየተከናወነ እንደሚገኝም ጠቁመዋል። ለአጠቃላይ ግንባታው 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት እንደሚፈጅም አስረድተዋል።

🛠️በአሁኑ ወቅት የሕንጻው መዋቅራዊ ሥራ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁንም ገልጸዋል። የውስጥ ዲዛይን፣ የማጠቃለያ እና የኢንስታሌሽን (ዝርጋታ) ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም አብራርተዋል።

📅አጠቃላይ የግንባታ ሥራውን እስከ ሰኔ መጨረሻ ድረስ ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ አገልግሎት ለማስጀመር በትኩረት እየተሠራ መኾኑን አስረድተዋል።

💻ግንባታው ተጠናቅቆ ሥራ ሲጀምር አገልግሎቶችን በተማከለ እና በዲጂታል መንገድ በመስጠት የደንበኞችን እርካታ እንደሚያረጋግጥ ታምኖበታል ነው ያሉት።

ከአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በክልሉ በሦሥት ዙር 38 መሶብ የአንድ ማዕከላትን አስገንብቶ ሥራ ለማስጀመር ወደ ተግባር ተገብቷል።

#አሚኮ_ዜና #የአንድ_መሶብ_አገልግሎት_ሥራ #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ

ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአስተማማኝነቱ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል!
Next articleአረንጓዴ አሻራ የቡና እና ፍራፍሬ ምርቶችን የጨመረ ሁነኛ የኢኮኖሚ ምንጭ ኾኗል።