አረንጓዴ አሻራ የቡና እና ፍራፍሬ ምርቶችን የጨመረ ሁነኛ የኢኮኖሚ ምንጭ ኾኗል።

5

 

ፍኖተሰላም: ሰኔ 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎጃም ዞን በአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ከ2 ሚሊዮን በላይ የቡና እና የፍራፍሬ ችግኞችን ለመትከል እየተሠራ ነው። የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር የሀገሪቱን የደን ሽፋን ከማሳደግ ባሻገር የአርሶአደሮችን የቡና እና ፍራፍሬ ምርት በመጨመር የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እያደረገ ነው።

የምዕራብ ጎጃም ዞን በዚህ ዓመት በአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር የቡና እና የፍራፍሬ ችግኞችን በአምስት ወረዳዎች ላይ በክላስተር ለመሸፈን እየተሠራ መኾኑን የዞኑ ምክትል አሥተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኀላፊ አጉማሴ አንተነህ ገልጸዋል።

በተለይ የቡና እና የአቮካዶ ምርትን በስፋት ለማምረት ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ለዚህም ከችግኝ ዝግጅት ባሻገር የጉድጓድ ቁፋሮም ጭምር እየተከናወነ መኾኑን ነው መምሪያ ኀላፊው የጠቆሙት።
በዞኑ የቡና እና የፍራፍሬ ችግኝ በክላስተር ከሚተከልባቸው ወረዳዎች መካከል የፍኖተሰላም ከተማ አሥተዳደር አንዱ ነው።

በከተማ አሥተዳደሩ ከ245 ሄክታር በላይ መሬት ላይ ቡና እና አቮካዶን በክላስተር ለመትከል የዝግጅት ሥራ መጠናቀቁን የፍኖተሰላም ከተማ አሥተዳደር ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መንገሻ እንኳኾነ ገልጸዋል።

በከተማ አሥተዳደሩ የሚገኙ አርሶአደሮች ከዚህ በፊት በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብሮች በፍራፍሬ ልማት ተጠቃሚ በመኾናቸው ለልማቱ ከፍተኛ የኾነ መነቃቃት እየተፈጠረ ስለመኾኑም ነው ያነሱት።

በምዕራብ ጎጃም ዞን በዚህ ዓመት እስካሁን ከ134 ሚሊዮን በላይ የሚኾኑ የደን የአትክል እንዲሁም የቡና እና የፍራፍሬ ችግኞችን በ13 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ለመትከል ሁለንተናዊ ዝግጅት ተደርጓል።

#አሚኮ_ዜና #የአረንጓዴ_አሻራ_ሥራ #ምዕራብ_ጎጃም #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article🏢የጎንደር ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ግንባታ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ይጠናቀቃል።
Next article🕊️በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በሺህዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን ተቀብለዋል።