አስተማማኝነቱ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል!

6

 

ባሕር ዳር:ሰኔ 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በቅርቡ የወጡ የደኅንነት ጥናቶች እንደሚያመለክቱት የመረጃ ስርቆት ተጋላጭነት እየሠፋ በመምጣቱ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች “የይለፍ ቃል አስተማማኝነቱ እያበቃ ነው” የሚል ማስጠንቀቂያ እየሰጡ ነው።

የመረጃ መንታፊዎች ሠራተኞችን ለማታለል እውነተኛ የሚመስሉ የሐሰት መግቢያ ገጾችን በመጠቀም መረጃዎችን እየሰረቁ መኾናቸው ተነግሯል።

የተጠቃሚን መዘናጋት በመጠቀም የብዙ ደረጃ ማረጋገጫን (MFA) በመጥለፍ ወደ ተቋማት ምሥጢራዊ መረጃ ሰርገዉ መግባት መቻላቸው የችግሩን አሳሳቢነት ጨምሮታል።

በተለይ ሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) የሳይበር ወንጀለኞች የሚልኳቸውን መልዕክቶች ይበልጥ አሳማኝ እንዲኾኑ እና ሰዎችን በቀላሉ እንዲያታልሉ ትልቅ እገዛ እያደረገላቸው እንደሚገኝ ተመልክቷል።

የይለፍ ቃላት የተፈጠሩት ሠራተኞች በቢሮ ውስጥ ብቻ በሚሠሩበት ዘመን እንደነበር ያስታወሰው ጥናቱ አኹን ግን ሥራ በየትኛውም ቦታ እና በግል መሣሪያዎች ጭምር የሚከናወን በመኾኑ የቆዩት የደኅንነት ፖሊሲዎች በቂ አለመኾናቸውን አመልክቷል።

ኢንሳ የ2025 የቲም ቪወር (TeamViewer) ጥናትን መሠረት በማድረግ 80 በመቶ የሚኾኑ ሠራተኞች ከመግቢያ መረጃ ጋር የተያያዘ ችግር እንደገጠማቸው አስነብቧል።

ውስብስብ የይለፍ ቃል ሕጎችም ተጠቃሚዎች መረጃቸውን ደኅንነቱ ባልተጠበቀ ቦታ እንዲያስቀምጡ እየገፋፏቸው መኾኑ ተጠቅሷል።

የዘርፉ ባለሙያዎችም ተቋማት በባዮሜትሪክስ (የጣት አሻራ እና የፊት ገጽታ) ላይ ወደሚሠሩ “ፓስኪዎች” (Passkeys) እንዲሸጋገሩ መክረዋል።

ይህም የመረጃ መንታፊዎች መረጃን ቢሰርቁ እንኳን ያለ ተጠቃሚው መሣሪያ መጠቀም ስለማይችሉ ጥቃቱን በከፍተኛ ኹኔታ እንደሚቀንሰው ነው የጠቆሙት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል የወባ በሽታ የሚያጠቃቸው አካባቢዎች ተለይተው የመከላከል ሥራዎች እየተሠሩ ነው።
Next article🏢የጎንደር ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ግንባታ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ይጠናቀቃል።