
ባሕር ዳር: ሰኔ 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ቆላማ አካባቢዎች የወባ በሽታ የክረምት መግባት እና የክረምት መውጫ ወቅቶች ላይ በስፋት ይከሰታል፡፡
በእነዚህ እና በሌሎች አካባቢዎችም በሽታው እንዳይከሰት የመከላከል ሥራው እየተከናወነ ይገኛል፡፡
የጃዊ ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መንበር ግርማ በክልሉ 10 ከፍተኛ የወባ በሽታ ከሚከሰትባቸው ወረዳዎች ውስጥ አንዱ የጃዊ ወረዳ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
ከጤና ሚኒስቴር በእርዳታ የተገኘን የወባ ትንኝ መከላከያ የአልጋ አጎበር ለሁሉም ቀበሌዎች ማሰራጨት ተችሏል ያሉት ኀላፊው በአጠቃቀም ዙሪያም የጤና ባለሙያዎች የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እየሠሩ መኾናቸውን አብራርተዋል፡፡
ጤና ጣቢያ መር የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል። ኹሉንም ትኩሳት ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎችን በዘመቻ የመመርመር እና የማከም ሥራ በ14 ቀበሌዎች ላይ እየተሠራ ነው ብለዋል። በቂ ግብዓት እየቀረበ መኾኑንም ተናግረዋል።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ኀላፊ አየለ አልማው በአሥተዳደሩ አምስት በላይ ወረዳዎች የወባ በሽታ በስፋት የሚከሰትባቸው መኾናቸው ተለይቶ የመከላከል ሥራው በትኩረት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡
የወባ ትንኝ መከላከያ ኬሚካል ርጭት በዚገም እና አየሁ ጓጉሳ ወረዳዎች በተመረጡ ቀበሌዎች መካሄዱን ገልጸዋል። የአልጋ አጎበር ስርጭት በጓንጓ፣ በቻግኒ ከተማ አሥተዳደር፣ በዳንግላ፣ በጃዊ እና በከፊል ባንጃ አካባቢ ተሠራጭቷል ብለዋል፡፡
የማከሚያ ግብዓት በሁሉም ጤና ጣቢዎች በበቂ ሁኔታ ቀርቧል ነው ያሉት፡፡ የግብዓት እጥረት እንደማያጋጥማቸውም ገልጸዋል፡፡ ማኅበረሰቡም የመከላከያ መንገዶችን በአግባቡ እንዲተገብር አሳስበዋል።
በአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የወባ ፕሮግራም አሥተባባሪ ዳምጤ ላንክር ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ በክልሉ የበልግ ወራት ላይ አነስተኛ የወባ ስርጭት መኖሩን ገልጸዋል። የክረምት መግቢያ እና መውጫ ወራት ላይ ግን የወባ በሽታ በስፋት ይከሰታል ነው ያሉት።
ምሥራቅ ጎጃም፣ ምዕራብ ጎጃም፣ አዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር፣ ሰሜን ጎጃም፣ ባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር፣ ደቡብ ጎንደር ዞን፣ ማዕከላዊ ጎንደር እና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች 91 በመቶ የክልሉን የወባ ሥርጭት ይሸፍናሉ ብለዋል። ከእነዚህ ዞኖች በወባ ስርጭት ቀዳሚ 40 ወረዳዎች 68 በመቶ የክልሉን ይሸፍናሉ። ወረዳዎቹም በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር፣ በደቡብ ጎንደር ዞን እና በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ውስጥ ይገኛሉ ነው ያሉት።
ባለፉት 11 ወራት በክልሉ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎች በወባ በሽታ መጠቃታቸው ያነሱት አስተባባሪው የወባ በሽታን ለመከላከል የወባ ባለሙያዎችን ጨምሮ ጉዳዩ ለሚመለክታቸው አካላት በአራት ክላስተር ሥልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል።
በ2018 ዓ.ም ከጤና ሚኒስቴር የተገኘውን 2 ሚሊዮን በላይ የአልጋ አጎበር ወባ በስፋት ለሚከሰትባቸው አካባቢዎች መሠራጨቱን ገልጸዋል።
ችግሩ በከፈባቸው 16 ወረዳዎች የኬሚካል ርጭት እንዲካሄድ ኬሚካል ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መመደቡን አንስተዋል። የወባ በሽታ በስፋት ለሚከሰትባቸው አካባቢዎች ትኩረት መደረጉን ገልጸዋል።
ኹሉም ማኅበረሰብ የተሰጠውን አጎበር በአግባቡ እንዲጠቀም እና የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ እንዲያከናውንም አስገንዝበዋል። የወባ በሽታ ምልክቶች ሲሰማቸውም በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ የጤና ተቋም በመሔድ እንዲመረመሩ አሳስበዋል። ተመርምረው ወባ መኾኑ ሳይረጋገጥ ምንም አይነት መድኃኒት መውሰድ አይገባም ነው ያሉት።
ዘጋቢ፡- ሰለሞን ሰንታየሁ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
