የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያ ሴቶች ማህበር አባላት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የለውጥ እና ማሻሻያ ሥራዎችን ጎበኙ።

8
ባሕር ዳር: ሰኔ 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የክልሉን የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ያለው፣ ቀልጣፋ፣ ዘመናዊ፣ተደራሽ፣ ጊዜ እና ወጪ ቆጣቢ በማድረግ፣ ፍርድ ቤቶች የሕዝብ አመኔታን ያተረፉ እንዲሆኑ የሚያስችል የለውጥ እና የማሻሻያ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል።
በተለያየ ጊዜ ከፌደራል እና ከክልል የሚመጡ እንግዶች የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን የለውጥ ሥራዎችን ለመመልከት የቻሉ ሲሆን፣ በዛሬው እለትም የፍርድ ቤት ጉዳዮች አዘጋገብ እና የፍርድ ቤት የማሻሻያ እና የለውጥ ሥራዎች ላይ ለመወያያት በጠቅላይ ፍርድ ቤት የተገኙት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያ ሴቶች ማህበር የአማራ ክልል አባላት የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን የለውጥ ሥራዎች ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸውም፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት የዲጂታላይዜሽን ሥራዎች እና ስማርት ችሎቶችን፣ የዲጂታል አንድ ማእከል አገልግሎት፣ ግልጽ ችሎት የሚከናወንባቸውን የችሎት አዳራሾች፣ የጥሪ ማእከል እና ሌሎች የለውጥና ማሻሻያ ሥራዎችን ተመልክተዋል።
በተሠሩ የማሻሻያ ሥራዎች መደነቃቸውን የገለጹት የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎቹ፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የስማርት ችሎት አገልግሎት እና የኢ- ፋይሊንግ አገልግሎት በመስጠት ዜጎች ከዚህ ቀደም ፍትሕ ለማግኘት ይደርስባቸው የነበረውን እንግልት እና ወጪ በማስቀረት ፍትሕን ተደራሽ በማድረግ ሕግ መንግስታዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ባሻገር በጠቅላይ ፍርድ ቤት ባሕር ዳር ምድብ ችሎት ጉዳይ ኖሯቸው በአካል ለሚመጡ እና ሕጻናት ለያዙ እናቶች እራሱን የቻለ ማረፊያ ማዘጋጀቱ ሰብአዊነት የሚሰማው ተግባር መሆኑን እና ባለጉዳዮች ተቋሙን በእኔእነት እና በባለቤትነት ስሜት እንዲገለገሉበት የሚያስችል ሥራ መሆኑን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሠራቸው ሥራዎች ክልሉን እና የክልሉን ማኅበረሰብ የሚመጥኑ ኾነው አግኝተናቸዋል ያሉት ባለሙያዎቹ፣ ሌሎች ተቋማትም የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን አርአያነት ያለው ሥራ በተሞክሮነት በመጠቀም ለተገልጋዮቻቸው ምቾትን የሚሰጡ ፣ የተገልጋይን እርካታ ማረጋገጥ የሚችሉ ተቋማትን እንዲገነቡ እና ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶችን እንዲዘረጉ ጠይቀዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየክረምት በጎ ባሕሎቻችንን ወደ ላቀ መገለጫነት እናሻግራለን፡፡
Next articleበአማራ ክልል የወባ በሽታ የሚያጠቃቸው አካባቢዎች ተለይተው የመከላከል ሥራዎች እየተሠሩ ነው።