የክረምት በጎ ባሕሎቻችንን ወደ ላቀ መገለጫነት እናሻግራለን፡፡

4
ባሕር ዳር: ሰኔ 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያውያን ባለፉት የለውጥ ዓመታት ክረምት በመጣ ቊጥር የምንከውናቸው ሁለት አንኳር ባሕሎችን እየገነባን መጥተናል፤ ኢትዮጵያን አረንጓዴ ማልበስ እና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ብሏል።
ኢትዮጵያ የደን ሀብቷ እየተመናመነ፣ የአፈር መሸርሸር እና ድርቅ ተጋላጭነቷ እየጨመረ መምጣቱን በመገንዘብ መንግሥት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርን በሚሊዮን ችግኞች ተከላ በማብሰር ከጥቂት ዓመታት በፊት መጀመሩን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያንም ይህንን በጎ ጅምር እና የመዳረሻ ትልም በላቀ ደረጃ በመገንዘብ እና የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሩን በተነሣሽነት በመተግበር ዓለምን ያስደመሙ ስኬቶችን አስመዝግበናል፡፡ በሂደቱ የምግብ፣ የደን እና የውበት ችግኞችን በመትከል ዐሻራችን እያኖርን ኢትዮጵያን አረንጓዴ የማልበስ ባሕላችንን በእጅጉ አጎልብተናል፡፡
በየዓመቱ በርካታ ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል የዓለም ሕዝብን ከአምስት እጥፍ የሚበልጥ ከ48 ቢሊዮን ላይ ችግኞች ተክለናል፤ በዚህም የኢትዮጵያን የደን ሽፋን ትርጒም ባለዉ መጠን አሳድገናል፤ ለምግብ ሉዓላዊነታችን መሠረት መጣል ጀምረናል፤ የፍራፍሬ የወጪ ንግዳችን አሳድገናል ነው ያለው።
ከሁለት ዓመታት በፊት ይፋ በተደረገ የጥናት ውጤት መሠረት የደን ሽፋናችን እጅግ ከተመናመነበት በከፍተኛ ፍጥነት አገግሞ ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ አድጓል፡፡
በልዩ ኹኔታ የኢትዮጵያውያንን የተቀናጀ እና የተሰናሰነ ተነሣሽነት በሚጠይቁ የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሮችም የዓለምን ትኩረት በሳበ መልኩ ሚሊዮኖች በአንድ ጀምበር እየወጣን በመትከል የራሳችንን ክብረ ወሰን በራሳችን ደጋግመን እያሻሻልን መጥተናል፡፡
በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የተከልናቸው የምግብ፣ የደን እና የውበት ችግኞች የኢትዮጵያን ኹለንተና የሚቀይሩ፣ የምግብ ሉዓላዊነታችንን የሚያረጋግጡ፤ የአበባ እና ፍራፍሬ ወጪ ንግዳችንን ዕድገት እየለወጡ ያሉ የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም ዐቅም ያጎለበቱ ናቸው ብሏል።
ይህ ክረምት በመጣ ቊጥር በንቅናቄ የሚከናወን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ባሕል የበለጠ እንዲጠናከርና እንዲጎለብት በትጋት መሥራታችንን እንቀጥላለን፤ ኢትዮጵያን አረንጓዴ በማልበስ ንጹሕ አየር ለዓለም እናበረክታለን ነው ያለው፡፡ ዘንድሮም የራሳችንን ክብረ ወሰን በራሳችን የላቀ የሚሊዮኖች ተሳትፎ በማሻሻል ጭምር ከ8 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን እንተክላለን፡፡
የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም ሌላኛዉ ዐዲስ እያደገ የመጣ ልምምዳችን ነው፡፡ ወጣቶች ዕውቀታቸዉን እና ከትምህርት የተረፈ ጊዜያቸውን፣ ባለሀብቶች ደግሞ ሀብታቸውን በማዋጣት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያሉ ዐቅመ ደካማ ወገኖችን ቤት በመገንባት፣ ማዕድ በማጋራት እጅግ የተዋጣለት ልምምድ አዳብረዋል፡፡
የመንግሥት ተቋማትም በቁጠባ ከሚጠቀሙት ሀብታቸው በማዋጣት ይህንን የበጎ አድራጎት ልምድ የማስፋት እና ወደ ላቀ ባሕል ደረጃ የማሳደግ ኃላፊነትን እየተወጡ ይገኛሉ፡፡
በለውጡ ዓመታት በአዲስ አበባ እና በክልሎች የበርካታ ዐቅመ ደካሞች ቤት ታድሷል፤ በአዲስ መልክ ተገንብቷል፤ ሕይወታቸዉ እንዲሻሻል ተደርጓል ነው ያለው። በከተሞች የተጀመረዉ የኮሪደር ልማት ወደ ገጠር ተስፋፍቷል። ኢትዮጵያውያን ችግሮቻችንን ተጋግዞ የመፍታት ባሕል እያዳበርን መጥተናል፡፡
የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወደየአካባቢያቸው በመሄድ እና በወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ታናናሾቻቸውን እያስተማሩ፣ እንደ ደም ልገሳ ያሉ ሕይወት አዳኝ ተግባራትን እያስተባበሩ፣ ዐቅመ ደካሞችን በማገዝ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መኾናቸውን አንስቷል።
በየክረምቱ በበጎ ልምድነት እያሳደግናቸው የመጡ የአረንጓዴ ዐሻራ እና የበጎ ፈቃድ ሥራዎች የበለጠ ሀገራዊ መገለጫችን እና ባሕላችን እንዲኾኑ ዘንድሮም ካለፉት ዓመታት የላቀ ተሳትፎ የሚጠይቅ ዕቅድ ተዘጋጅቷል፤ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል።
በተደመረ ዐቅማችን የኢትዮጵያን ዕቅድ በሚገባ ለማሳካት ቅድመ ዝግጅት ጨርሰን ወደ ትግበራ ገብተናል። ድላችንን በጋራ የምናበስርም ይኾናል ብሏል በመልዕክቱ።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየፌዴራል መንግሥት መስሪያ ቤቶች ኦዲት የማድረግ ሥራ በጥራት እየተከናወነ ነው።
Next articleየኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያ ሴቶች ማህበር አባላት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የለውጥ እና ማሻሻያ ሥራዎችን ጎበኙ።