የፌዴራል መንግሥት መስሪያ ቤቶች ኦዲት የማድረግ ሥራ በጥራት እየተከናወነ ነው።

3

 

አዲስ አበባ: ሰኔ 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገሪቱን የኦዲት ሥርዓት ማጠናከር ሀገራዊ ዕድገትን ለማረጋገጥ የጎላ ሚና እንዳለው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ ተናግረዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ26ኛ መደበኛ ሥብሥባው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የፌዴራል መንግሥት መስሪያ ቤቶች የ2017 በጀት ዓመት ሒሳብ የፋይናንሺያል፣ የሕጋዊነት እና የክዋኔ ኦዲት ሪፖርትን አዳምጧል።

ሪፖርቱን ያቀረቡት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ ባለፈው የበጀት ዓመት የፌዴራል ዋና ኦዲተር 163 ተቋማትን ኦዲት ማድረጉን ገልጸዋል።

የፌዴራል መንግሥት መስሪያቤቶችን ኦዲት የማድረግ ሥራ በጥራት ማከናወኑን የገለጹት ዋና ኦዲተሯ በተለይም ግኝቱ ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር የጥሬ ገንዘብ ጉድለት እየቀነሰ መምጣቱን ጠቅሰዋል። የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ መጠቀም ለተገኘው ውጤት አስተዋጽኦ ማድረጉን አስታውቀዋል።

በበጀት ዓመቱ በኦዲት ሥራው የግዥ አዋጅ እና አሠራርን አለመከተል፣ የግንባታ ውል ግልጸኝነት ችግር፣ የታክስ ግልጽነት መጉደል እና ያለአግባብ የተከፈሉ ክፍያዎች መኖር በበጀት ዓመቱ ያጋጠሙ ችግሮች መኾናቸውን ዋና ኦዲተሯ ጠቅሰዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ 6 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ያልተሠበሠበ ቀረጥ እና ታክስ የገቢ ሂሳብ መኖሩን የጠቀሱት ዋና ኦዲተሯ ይህም በገቢ አሠባሠብ ሥራው ላይ ያለውን ክፍተት እንደሚያሳይ ተናግረዋል።

የፌዴራል ዋና ኦዲተር እየተስተዋሉ ያሉ የኦዲት ችግሮችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር እና መፍትሄዎችን በማስቀመጥ ችግሮችን ለመቅረፍ እየሠራ ያለውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

#አሚኮ_ዜና #የኦዲት_ሥራ #ኢትዮጵያ

ዘጋቢ፦ ሰለሞን አሰፌ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የጤና ተቋማትን በማዘመን ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ ተችሏል” አቶ አብዱልከሪም መንግሥቱ