
ኢትዮጵያውያን ሀገር በጠራቻቸው፣ ኑ ባለቻቸው ጊዜ ተነስተው መገስገስ፣ እናታቸው ኑ ወደ አለችበት ሥፍራ ሁሉ መድረስ ያውቁበታል።
ሀገር ጠርታቸው የቀሩበት፣ ሀገር ድረሱ ብላቸው የዘገዩበት፣ ሀገር ኑ ብላቸው ፊታቸውን ያዞሩበት፣ እፈልጋችኋለሁ ብላቸው የራቁበት ዘመን የላቸውም።
ሀገር ስትጠራቸው ሠንደቅ ዓላማዋን ለብሰው በፍቅር ይገሰግሳሉ፤ በተባሉበት ጊዜ ቦታ በፍጥነት ይደርሳሉ። ሀገር እየጠራቻቸው ተነስተው ጠላቶቿን ድል ነስተዋል፤ በታሪክ የከበረውን ገድል ፈጽመዋል፤ ሀገር እየጠራቻቸው ድንበሯን አጥረው፣ ዳሯን እሳት አድርገው ኖረዋል። ሊደፍሯት የከጀሉትን ሁሉ ድባቅ መተዋል።
አሁንም ኢትዮጵያ ሁሉንም ልጆቿን ጠርታለች። ለምክክር ለውይይት ተሠብሠቡ ብላለች። ልጆቿም የእናታቸውን ጥሪ አክብረው ለምክክር ተሠባሥበዋል፤ በአንድ አዳራሽ ከትመዋል። ቀድሞ ድንበሬን አስከብሩ፣ የጠላቶቼን ቅስም ስበሩ፣ ወሰኔን በጀግንነት እጠሩ እያለች ስትጣራ በአንድነት የተሠባሠቡላት ልጆቿ ዛሬ ደግሞ በምክክር የውስጥ ችግራችሁን ፍቱ፣ ጥልና ጥላቻን አርቁ፣ ሰላምን በምድሬ ላይ አረጋግጡ ብላ ስትጣራ ከአራቱም ንፍቅ ተጠራርተው ተገናኝተዋል።
እንደቀደመው ሁሉ ኢትዮጵያን አሸናፊ ሊያደርጓት፤ ከእነ ክብሯ ሊያኖሯት፤ በክብር እና በሞገስ ሊጠብቋት፤ ሰላም እና አንድነቷን ሊጠብቁላት ለምክክር ተቀምጠዋል፤ የእናታቸውን አደራ ሊወጡ በአንድ አዳራሽ ሥር ተሠባሥበዋል።
ኢትዮጵያውያን እየመከሩ ነው። ከዚህ ቀደም በታሪካቸው ያልነበረውን ታላቁን ጉባኤ እያካሄዱ ነው። በታሪካቸው ሌላኛውን ታላቅ ታሪክ እየጻፉ ነው። እስካሁን ያልተሳተፉት ኢትዮጵያውያን ተሳትፈዋል፤ እስካሁን ያልተካተቱት ተካትተዋል። ታሪካቸውም በጋራ የጻፉት፣ በጋራ የሚናገሩት፣ በጋራ የሚያስተላልፉት እና ለልጅ ልጅ የሚያወርሱት ይኾናል።
ከሐመር ካራ ብሔረሰብ የመጡት ሙዶ አኮ በምክክር ጉባኤው ባደረጉት ንግግር ለብዙ ዘመናት እንደእኛ ያሉ ሴቶች ታሪክን ከሩቅ ቆመን ስንመለከት ኖረናል። ሌሎች ይናገሩ ነበር፤ ሌሎች ይወስኑ ነበር፤ እኛ ግን ከሩቅ ቆመን እናይ ነበር ብለዋል።
ወንድሞቻችንን ቀብረናል። እንባችንን አፍስሰናል። ሰላም መቼ ይመጣ ይኾን? ብለን ብዙ ጊዜ ጠይቀናል። ዛሬ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገሬ እንድናገር ጠርታኛለች ነው ያሉት። አዎን እሳቸውን ብቻ ሳይኾን ኢትዮጵያ ሁሉንም ልጆቿን ጠርታለች።
ይህ የእኔ ብቻ ድምጽ አይደለም፤ ይህ ከሩቅ ያሉ ሴቶች እና እናቶች ድምጽ ነው። የማይሰማ እና የማይጠየቅ የነበረ ነገር ግን ኢትዮጵያን ከልብ የሚወድ የብዙ ሰው ድምጽ ነው ይላሉ።
ዛሬ ኢትዮጵያ እያዳመጠች ነው፤ ባለመነጋገራችን ብዙ ነገር አጥተናል፤ ያገኘነው ግን እንባ፣ ሀዘን፣ ጥላቻ እና በቀል ነው ብለዋል ሙዶ አኮ። በዚህ ንግግራቸው የዘመናት የኢትዮጵያውያን የልብ ሐቅ ይገለጻል።
እሳት ቤት መገንባት ቢችል ኖሮ ኢትዮጵያ ከዘመናት በፊት ተገንብታ ትጨርስ ነበር። ነገር ግን ቤት የሚገነባው እጆች ሲተባበሩ፣ ልቦች ሲግባቡ እና ሰዎች ሲደማመጡ ነው፤ ኢትዮጵያ የእኔ፣ የእናንተ ፤ የእኛ ናት፤ የሁላችንም ናት።፤ ስለዚህ ወገኖቼ፣ ይዛችሁ የመጣችሁትን ቁጣ እና ቋጠሮ ይዛችሁ አትመለሱ። ተመካክራችሁ ፍቱ እንጂ ነው ያሉት።
ማን ያሸንፋል? ብለን አንጠይቅ፤ ኢትዮጵያን አሸናፊ እናድርግ፤ የእኔ እና የብዙ እናቶች ሕልም ይህ ነው ኢትዮጵያን አሸናፊ እናድርግ ይላሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ.ር) ምክክሩ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ የገዘፈ ዓላማ ያለው፣ የገዘፈ ተግባር የሚፈጽም እና ለአፍሪካ ምሳሌ የሚኾን ነው ይላሉ። ለዘመናት የሚታወስ ታሪክ ለመጻፍ ዕድል የሚሰጥ ነው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በርከት ያሉ ፈተናዎችን አሳልፈናል፤ ይህን ፈተና ወደ ዕድል መቀየር ከቻልን ለልጆቻችን መልካም ነገር እንፈጥራለን ነው የሚሉት።
አንዳንድ ዕድሎችን በአግባቡ ካልተጠቀምንባቸው ደጋግመው አይገኙም፤ የተሰጠንን ዕድል እንጠቀምበት ነው ያሉት። በኀይለ ቃል ተጀምሮ በኀይል እርምጃ የሚደመደመውን ፖለቲካ ለመቀየር ይሄን አጋጣሚ መጠቀም አለብን ይላሉ።
ምንም ጉዳይ ቢያጨቃጭቀን እንዲህ ባለው ጉባኤ መፍታት እንችላለን፤ ኢትዮጵያን ያጸናት ንግግር፣ ሽምግልና እና ይቅርታ ነው፤ የንግግር ባሕላችን ኢትዮጵያን አጽንቷል፤ ይሄን ጠብቀን ከመከርን የበለጸገች ኢትዮጵያን ለልጆቻችን እናወርሳለን ነው ያሉት።
ለኢትዮጵያ ብላችሁ ምከሩ፣ ለዛሬ ሳይኾን ለነገ ምክሩ፣ ለእናንተ አትምከሩ፣ ለልጆቻችሁ ምክሩ፣ እያንዳንዱ ተመካካሪ የነገ ልጆቹን እያሰበ ይመካከር ይላሉ። ማንም ሳይጎዳ በጋራ መጠቀም የምንችልባቸውን ጉዳዮች አንስተን ከተወያየን፣ ለእኔ ሳይኾን ለእኛ ካልን ለኢትዮጵያ ብለን ከተመካከርን ስኬታማ ምክክር እናደርጋለን ነው ያሉት። ከልብ ተመካክራችሁ ለኢትዮጵያ የሚበጀውን አድርጉም ብለዋል።
#AMECO #National_Dialogue #Ethiopia 🇪🇹
#ባሕር_ዳር፡ሐምሌ11/2018 ዓ.ም
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
