📢 ከአማራ ሕዝብ ታሪካዊ ጠላት ጋር የሚሠራው ጽንፈኛ ቡድን የሕዝብ ጠላት ነው።

7

 

በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች የአማራን ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎችን ለማስመለስ ነው የወጣነው ሲሉ ይደመጣሉ። በሕዝብ ስም የወጡት ታጣቂዎች የሚናገሩት እና ተግባራቸው ግን ለየቅል ነው።

ጥያቄህን እናስመልሳለን፤ መብትህን እናስከብርልሃለን ያሉትን የአማራ ሕዝብ የመከራ ጽዋን እንዲጎነጭ፤ ተወልዶ ባደገበት፤ እትብቱ በተቀበረበት ቀዬ እንዳይኖር፤ ሠርቶ እንዳይለወጥ፤ በሀዘን እና በደስታ ከቤተሰቡ ጋር እንዳይገናኝ በመከራ እንዲሰቃይ ማድረጋቸውን ሕዝቡ በተደጋጋሚ የሚያነሳው ጉዳይ ነው።

ግጭቱ ሕዝቡ ከቦታ ወደ ቦታ እንዳይንቀሳቀስ፤ ልጅ እናቱን እንዳይጠይቅ፤ እናት ልጇን እንዳትጎበኝ፤ ወላድ እናቶች በምጥ ወቅት ወደ ሆስፒታል እንዳይሄዱ፤ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ እንዳይገኙ አድርጎ ቆይቷል።

ታጣቂዎቹ ከአማራ ሕዝብ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ወዳጅነት በመፍጠር ሕዝቡ ሰላም እንዳያገኝ እየሠሩ ነው።

የአማራ ሕዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ወንድሞቹ ጋር ሀገር እንዳጸና እየታወቀ አማራን ጨቋኝ በማድረግ የሀሰት ትርክትን በመፍጠር፤ የአማራ ሕዝብን ወሰን በኃይል በመንጠቅ፤ በሥልጣን ዘመኑ የአማራ ሕዝብ በመሠረተ ልማት ግንባታ፤ በኢኮኖሚ እምርታ እንዳይጠቀም ኢኮኖሚያዊ በደል በመፈጸም፤ ከሥልጣን ሲወርድም በሰሜኑ ጦርነት በማይካድራ፣ በጭና፣ ጠለምት እና ራያ የዘር ጭፍጨፋን ከፈጸመው ከሕገ ወጡ የሕወሃት ቡድን እና ከሌሎች ሕገ ወጥ ቡድኖች ጋር በመጣመር እየሠሩ መኾናቸውን የጽንፈኛ ቡድኑ አባላት በተደጋጋሚ ሲገልጹ ይስታዋላል።

ይህ ድርጊት ጽንፈኛው ቡድን ለራሱ ጥቅም ወደ ጫካ እንደወጣ የሚያረጋግጥ እና የሕዝብ ጠላት መኾኑን የሚያስመሰክር ነው።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በቅርቡ በደብረ ማርቆስ ንጉሥ ተክለሃይማኖት አውሮፕላን ማረፊያ ምርቃት ላይ ባደረጉት ንግግር በአማራ ሕዝብ ጥያቄ እየማሉ ሕዝብን የሚያደናግሩ ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር የሚሠሩ ታጣቂዎች በመኖራቸው ሕዝቡን ለስቃይ ዳርገውታል ብለዋል። ሕዝብን እየጎዱ የሚገኙ አሜካላዎችን በመታገል ሰላምን ማጽናት እንደሚገባ አሳስበዋል። ሕዝቡ አሜካላዎችም በመታገል ሰላሙም ማረጋገጥ አለበት ነው ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በደብረ ማርቆስ ንጉሥ ተክለሃይማኖት አውሮፕላን ማረፊያ ምርቃት ላይ ባደረጉት ንግግር በዓባይ ሸለቆ፤ አሊ ዶሮ አካባቢ የመሸገውን፤ ወደ አዲስ አበባ አላሻግር ያለውን ሽፍታ በጋራ ታግለን ማስወገድ ሲገባን ተጨማሪ ሽፍቶችን ማበራከት ተገቢ አይደለም ብለዋል።

የትም ቦታ ያለውን ሽፍታ ተሰናስሎ በማስወገድ የሕዝብን ሰላም እና ልማት ማረጋገጥ ሲገባ በየሠፈሩ ሽፍቶች እየተበራከቱ ሰዎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው እንዳይሠሩ አድርገዋል ነው ያሉት።

ለምለም ሀገር ይዘን ተግባብተን እና ተዋደን ሀገርን መሥራት፤ ባንግባባም ተወያይተን፣ ተነጋግረን ሳንጋደል አብረን መኖር ሲገባን፤ ክፉ ክፉውን የምንስብ መልካሙን የምንገፋ መኾን የለብንም ብለዋል።

የሚለያዩ ነገሮችን በውይይት በመፍታት፤ በትልቅ ጉዳይ ላይ በመሠብሠብ እና በመተባበር የሁሉም ሰው የጋራ መሻት የኾነውን ሰላም እና ልማት በጋራ ለማስፈጸም መጣር ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የማያግባቡ ነገሮችን በሰላማዊ እና በሥለጠነ የፖለቲካ አግባብ መነጋገር ይቻላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚያ ውጭ ያለው አማራጭ ኢትዮጵያን አይጠቅምም ብለዋል።

ግጭት ሊበቃን ይገባል በጋራ መወሰን ያስፈልጋልም ነው ያሉት። መንግሥት ከሕዝብ ጋር በመኾን ሊወያዩ እና ሊነጋገሩ የሚፈልጉ አካላትን ለመቀበል የሰላም በሩ ሁልጊዜም ክፍት መኾኑንም ተናግረዋል።

#አሚኮ_ዜና #ሰላም #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ 🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_11_2018 ዓ.ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየተፈራ ኃይሉ ጠቅላላ ሆስፒታል የሲቲ ስካን ማሽን እና ሌሎች የሕክምና መሣሪያዎች እንዲሟሉለት ሁሉም ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ።
Next article“ኢትዮጵያ ሁሉንም ጠርታለች”