
በሰቆጣ ከተማ የሚገኘው የተፈራ ኃይሉ ሆስፒታል ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ጠቅላላ ሆስፒታል ማደጉ ይታወሳል። ሆስፒታሉ የሲቲ ስካን ማሽን እንዲኖረው እና ሌሎች ግብዓቶች እንዲሟሉለት ለማስቻል በአዲስ አበባ ውይይት ተካሂዷል።
የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንታይቱ ካሴ ሆስፒታሉ ሲቲ ስካን ቢመደብለትም መሳሪያውን ወደ ሥራ ለማስገባት ተጨማሪ መሟላት የሚገባቸው ግንባታዎች አስፈልገዋል ብለዋል። በመኾኑም ሆስፒታሉን በግንባታ እና በሕክምና ቁሳቁስ ለማሟላት የክልሉ ጤና ቢሮ እየሠራ ይገኛል ነው ያሉት።
የዋግኽምራ ብሔረሰብ ጤና መምሪያ ኀላፊ አሰፋ ነጋሽ ጤና መምሪያው ግንባታውን ለማከናወን ከድጋፍ አድራጊዎች፣ ከአካባቢው ተወላጆች፣ ከባለሃብቶች እና መንግሥታዊ ካልኾኑ ድርጅቶች ሃብት እያፈላለገ ይገኛል ብለዋል።
በተፈራ ኃይሉ ጠቅላላ ሆስፒታል የሲቲ ስካን መሳሪያ ሥራ አለመጀመር ታካሚዎችን ወደ ደሴ፣ ባሕር ዳር እና ወደ ሌሎች ሆስፒታሎች ሪፈር ለመላክ አስገድዷል ነው ያሉት።
ይህ ደግሞ ታካሚዎችን ለእንግልት እና ለወጭ ከመዳረግ ባለፈ ሪፈር በሚላክበት ጊዜ በአካባቢው ባጋጠመው የጸጥታ ችግር አምቡላንሶች በታጣቂዎች ተወስደዋል፤ በዚህም ከመጋቢት 2018 ዓ.ም ጀምሮ የሕክምና ሪፈር የሚጻፍላቸውን ታካሚዎች ማጓጓዝ አልተቻለም ብለዋል።
ለሆስፒታሉ የተመደበውን ሲቲ ስካን ወደ ሥራ ማስገባት ቢቻል የተሻለ ሕክምና ለመስጠት እና ሪፈር የሚጻፍላቸውን ታካሚዎች ቁጥር መቀነስ እንደሚቻል ተናግረዋል።
ከሲቲ ስካን ማሳረፊያ ግንባታ በተጨማሪ
ለሆስፒታሉ አገልግሎት መሻሻል የሚያግዙ ሌሎች ግብዓቶችን ለማሟላት የሚያስችሉ የፋይናንስ ድጋፍም ተጠይቋል።
ለህሙማን ሕይወት ለመድረስ ባለሃብቶች፣ መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች እና ተቋማት ሆስፒታሉ የገጠመውን ችግር ለመቅረፍ ርብርብ እንዲደርጉ ጥሪ ቀርቧል።
#አሚኮ_ዜና #የተፈራ_ኃይሉ_ሆስፒታል #ሰቆጣ #አዲስአበባ #ሐምሌ_11_2018ዓ_ም
ዘጋቢ፦ ተመስገን ዳረጎት
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
