
የግጭትን ኪሳራ፤ የሕዝብን ሰቆቃ፤ የሀገርን ውድመት፤ የንጹሐንን ሞት የአክሳሪ መንገድን ጥፋት ተረድተው የሰላምን ፈለግ የተከተሉ ታጣቂዎች ለራሳቸው እና ለሕዝባቸው ውለታን ውለዋል።
የሰላምን አሥፈላጊነት ተገንዝበው፤ ሰላምን ሽተው፤ የሰላም አማራጭን የተቀበሉ ታጣቂዎች ዛሬ ላይ ለሰላም እየሠሩ ነው። የአማራ ሕዝብ ችግር በግጭት እንደማይፈታ ያመኑ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን ተቀብለው ገብተዋል። ከክልሉ መንግሥት ጋር የሰላም ሥምምነትም ተፈራርመዋል።
በተሳሳተ የትግል አቅጣጫ ተሰልፈው ሕዝብ መከራ እና በደል መቀበሉን፤ በአካባቢው በነጻነት እንዳይንቀሳቀስ መደረጉን፤ ለማኅበራዊ እና ለኢኮኖሚያዊ ጫና መጋለጡን በመገንዘባቸው የሰላምን አማራጭ መቀበላቸውን ታጣቂዎች በተደጋጋሚ ገልጸዋል።
ጥያቄዎችን በጦር መሥሪያ ሳይኾን በውይይት እና በምክክር መፍታት እንደሚገባም ያምናሉ። የመረጡት የትጥቅ ትግል መንገድ ዘመኑን የዋጀ እንዳልኾነም ተናግረዋል። የሰላምን አማራጭ የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎች በጫካ የሚገኘውን የታጣቂ ቡድን ሚዛን አዛብተዋል፤ ሤራውን አጋልጠዋል፤ ምስጢሩን ዘርዝረዋል።
ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን በመቀበል የታየውን አንጻራዊ ሰላም ወደ ፍጹም ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲቀይሩ፤ ለሕዝብ የሰላም እፎይታን እንዲሰጡ ለቀድሞ ጓዶቻቸው ተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርቡ ይደመጣል።
የሰላምን መንገድ መከተል የክልሉን ሕዝብ የሚያሻግር፤ ሰላም እና መረጋጋት የሚያመጣ፤ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መነቃቃትን የሚፈጥር፤ የልማት ሥራዎችን የሚያሳልጥ፤ የኢኮኖሚ እምርታን የሚያስመዘግብ ነው። ሰላምን መምረጥ የዘመኑ ጀግንነት መኾኑንም መስክረዋል።
የክልሉ መንግሥት ከአፋሕድ ጋር የሰላም ሥምምነት በፈጸመበት ወቅት የአፋሕድ ከፍተኛ አመራር ማስረሻ ሰጤ ባደረጉት ንግግር በጦርነት ተጀምሮ በጦርነት ያለቀ ታሪክ የለም መጨረሻው የሰላም መንገድ ነው ብለዋል። በክልሉ ያለው ግጭት በሰላማዊ መንገድ ካልተጠናቀቀ የአማራ ሕዝብን ሰቆቃ የሚያራዝም መኾኑን መግለጻቸው ይታወሳል።
ችግሮችን በውይይት እና በምክክር መፍታት ብልጠት እና የፖለቲካ ጥበብ እንጅ ሽንፈት አይደለም ነው ያሉት። ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር የሚደረግ ግንኙነት አጥፊ መኾኑንም ገልጸዋል።
ትጥቅ አንግተው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች የሰላምን አማራጭ እንዲቀበሉ፤ ችግሮችን በውይይት እንዲፈቱ እና ግጭቱ በአማራ ሕዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን ዘርፈ ብዙ ኪሳራ እንዲያስቆሙም ጥሪ አቅርበዋል።
ሌላኛው የቀድሞ የአፋሕድ መሪ ኮሎኔል ፈንታው ሙሃባ ከአሚኮ ጋር ባደረጉት ቆይታ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር መሰለፍ ባንዳነት ነው ብለዋል።
ግጭቱ መሠረተ ልማቶች እንዲወድሙ፤ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ፤ ሕዝብ በየመንገዱ እንዲዘረፍ፤ ለከፋ ሰቆቃ እንዲጋለጥ፤ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እንዲደርስበት አድርጎታል ነው ያሉት። ጥያቄዎች በውይይት እና በንግግር ይፈታሉ፤ የሰላምን አማራጭ መከተል ያስፈልጋልም ብለዋል።
በሕዝብ ላይ የደረሰውን ግፍ በመመልከት የሰላም አማራጭ መቀበላቸውን ተናግረዋል። የሰላም አማራጭ የአሸናፊነት መንገድ መኾኑንም ጠቁመዋል። የአማራ ሕዝብ ጦርነት የመሸከም አቅም የለውም፤ ሰላምን ማጽናት ያስፈልጋል ነው ያሉት። በጫካ የሚገኙ ታጣቂዎች የሰላምን አማራጭ እንዲቀበሉም ጠይቀዋል።
#አሚኮ #ሰላም #አማራክልል #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ባሕር_ዳር፡ ሐምሌ11/2018 ዓ.ም
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
