“የጤና ተቋማትን በማዘመን ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ ተችሏል” አቶ አብዱልከሪም መንግሥቱ

3

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የሚገኙ የጤና ተቋማትን የአገልግሎት አሰጣጥ እና የተቋማት ማስፋፊያ ሥራዎችን የክልሉ እና የከተማ አሥተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች እና ባለሙያዎች የመስክ ምልከታ አካሂደዋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኅላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ እንዳሉት ኅብረተሰቡ ጥራት ያለው እና ፍትሐዊ የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ የጤና ተቋማትን የመሠረተ ልማት የማስፋፋት እና የማደስ ሥራ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል። በክልሉ ከ930 በላይ ጤና ጣቢያዎች እና ከ100 በላይ ሆስፒታሎች መኖራቸውን የገለጹት ቢሮ ኅላፊው ተቋማቱን ለታካሚዎች ምቹ፣ ጽዱ እና ማራኪ የማድረግ ሥራም ተጠናክሮ ቀጥሏል ነው ያሉት።

​በተለይም የእናቶች እና የሕጻናትን ጤና የመጠበቅ እንዲሁም ተላላፊ እና ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎችን ለመከላከል በትኩረ እየተሠራ ነው ብለዋል። የጤና መረጃ ሥርዓቱን ዲጂታላይዝ በማድረግ አገልግሎቱን ከወረቀት ነጻ እና ቀልጣፋ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መኾኑንም ነው የተናገሩት።

የጤና አገልግሎትን በጥራት በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሠራም አረጋግጠዋል።

​የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ከተማዋን ዘመናዊ፣ ውብ እና ጤናማ ለማድረግ የመሠረተ ልማት ለማሟላት መሠራቱን ገልጸዋል። በዚህም ውጤታማ ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑን ነው የተናገሩት።

የጤና ጣቢያዎችን ደረጃ በማሳደግ እና በማዘመን ለሕጻናት እና እናቶች የተሻለ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ ነውም ብለዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ምክትል ኅላፊ ጌትነት አባት በከተማ አሥተዳደሩ 10 የጤና ተቋማትን የማዘመን ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል። በሁሉም የጤና ጣቢያዎች የተሻለ ላቦራቶሪ የማሟላት እና የግብዓት አቅርቦት ላይ ጥራት ለማምጣት እየተሠራም ነው።

በዚህም ለተሞክሮ የሚኾኑ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል። ዛሬም በከተማ አሥተዳድሩ ስር የሚገኙ ዳግማዊ ምኒሊክ ጤና ጣቢያ፣ ሽምብጥ እና ዓባይ ጤና ጣቢያዎች የተጎበኙ መኾናቸውን ነው የተናገሩት።

አዳዲስ ሕንጻዎችን መገንባት፣ ነባሮቹን ማደስ እና የጤና ጣቢያዎችን ደረጃ ወደ ሆስፒታል ለማሳደግ እየተሠራ መኾኑንም ነው ያስረዱት።

#አሚኮ_ዜና #የጤና_ተቋማትን_የማዘመን_ሥራ #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ

ዘጋቢ፦ሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ዝግባ የሕጻናት እና አረጋውያን መርጃ በጎ አድራጎት ድርጅት እርስ በእርስ መረዳዳትን ያሳየ ነው” አቶ ጎሹ እንዳላማው
Next articleየፌዴራል መንግሥት መስሪያ ቤቶች ኦዲት የማድረግ ሥራ በጥራት እየተከናወነ ነው።