“ዝግባ የሕጻናት እና አረጋውያን መርጃ በጎ አድራጎት ድርጅት እርስ በእርስ መረዳዳትን ያሳየ ነው” አቶ ጎሹ እንዳላማው

2

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል እና የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ዝግባ የሕጻናት እና አረጋውያን መርጃ በጎ አድራጎት ድርጅት እያከናወነ የሚገኘውን ሥራ ጎብኝተዋል።

በድርጅቱ ድጋፍ የሚደረግላቸው እሙሐይ ወርቄ በላይ እና አምሳ አለቃ ሽፈራው መንግሥቱ ዝግባ የሕጻናት እና አረጋውያን መርጃ በጎ አድራጎት ድርጅት ሲቸግረን የሚያጎርሰን፣ ሲጠማን የሚያጠጣን፣ ሲበርደን የሚያለብሰን ድርጅት ነው ብለዋል።

ድርጅቱ ባይኖር ያለጧሪ ጎዳና ላይ ወድቀን እንሞት ነበር ነው ያሉት። እያደረገላቸው ላለው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።

የዝግባ የሕጻናት እና አረጋውያን መርጃ በጎ አድራጎት ድርጅትሥራ አሥኪያጅ ስለሽ ጌታቸው በጎ አድራጎት ድርጅቱ በ2001 ዓ.ም መመሥረቱን አስታውሰዋል። አሁን ላይ በባሕር ዳር፣ እንጅባራ እና አዲስ አበባ ከ3ሺህ 590 በላይ ለከፋ ችግር ለተጋለጡ ሕጻናት፣ አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞች፣ ለተቸገሩ ሴቶች እና ወጣቶች ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ድርጅቱ ከአንድ ዓመት ሕጻን ጀምሮ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ኹሉን አቀፍ ድጋፍ የሚያደርግ ሀገር በቀል ድርጅት ነው ብለዋል።

ድርጅቱ ሥራውን የሚያከናውነው ምንም ዓይነት የውጭ እርዳታ ሳይጠብቅ ማኅበረሰቡን በማስተባበር፣ በገንዘብ፣ በሙያ እና በቁሳቁስ የሚያግዙ አጋሮችን በማስተባበር መኾኑን ገልጸዋል። ድርጅቱ በቋሚ ቅጥር እና በተለያዩ የሥራ ዘርፎች በርካታ ዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረጉንም አንስተዋል።

በቀጣይ ዓመታት ድርጅቱን ከሦሥት እጥፍ በላይ በማሳደግ ከ12 ሺህ በላይ ድጋፍ የሚፈልጉ ዜጎችን ለመርዳት ታቅዷል። ለዚህም ከተማ አሥተዳደሩ አሥፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ድርጅቱ መልካም የሰብዓዊነት ሥራ እየሠራ መኾኑን ተመልክተናል ብለዋል።

የነገ ሀገር ተረካቢ ሕጻናት እንክብካቤ እያገኙ እና እየተማሩ፤ በእርጅና ዘመናቸው መጦር ያለባቸው አረጋውያን እየተደገፉ፤ አካል ጉዳተኞች እና ታማሚዎች የሚረዱበት ማዕከል ኾኖ አግኝተነዋል ነው ያሉት። ለድርጅቱ መሥራቾች፣ ለድርጅቱ ሠራተኞች እና ድጋፍ ለሚያደርጉት ኹሉ ምሥጋና አቅርበዋል።

ድርጅቱ የውጭ ድጋፍ የማይፈልግ፤ የሀብት ምንጩ ከራሱ ከማኅበረሰቡ እና ወገን ለወገን የሚደረግ መኾኑ ለየት ያደርገዋል ነው ያሉት። የመንግሥት አቅጣጫም የውጭ እርዳታ ሳያስፈልግ እርስ በእርሳችን የመደጋገፍ ባሕላችንን ማሳደግ ነው ብለዋል።

ድርጅቱ እያከናወነ የሚገኘው የበጎ አድራጎት ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ከዚህም በላይ ማደግ እና መስፋት አለበት ብለዋል። ለዚህ ደግሞ የኹሉንም እርብርብ ይፈልጋል ነው ያሉት። ከተማ አሥተዳደሩም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

#አሚኮ_ዜና #የበጎ_አድራጎት_ሥራ #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ

ዘጋቢ፦አድኖ ማርቆስ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማራ ክልል ጤና ቢሮ ሕዝቡን የጤና ተጠቃሚነት የሚያረጋገጥ የሪፎርም ሥራ እያከናወነ ነው።
Next article“የጤና ተቋማትን በማዘመን ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ ተችሏል” አቶ አብዱልከሪም መንግሥቱ