
ባሕር ዳር: ሰኔ 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ለአፍሪካውያን ከአፍሪካውያን በላይ የሚቀርባቸው ወዳጅ የለም። አፍሪካውያን ችግሮቻቸውን በራሳቸው አቅም የመፍታት ጥበብ፣ ሥልጣኔ እና ታሪክ አላቸው።
አፍሪካውያን ስለራሳቸው የሚናገርላቸው፤ ስለራሳቸው የሚሠራላቸው፣ ስለ ራሳቸው የሚቆምላቸው የውጭ ኀይል አያስፈልጋቸውም። ሁሉንም በራሳቸው፤ ስለ ራሳቸው ማድረግ ይችላሉና።
ኢትዮጵያ አፍሪካ ለአፍሪካውያን ብቻ መኾን አለባት፤ አፍሪካውያን ስለ ራሳቸው መሠባሠብ፣ አንድ መኾን፣ ችግሮቻቸውን በራሳቸው መፍታት፣ የወደፊት ዕጣ ፋንታቸውን በራሳቸው መወሰን አለባቸው ብላ ታምናለች። ለዚህም ይኾን ዘንድ አፍሪካውያንን የሚያሠባሥብ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ፈጥራለች።
ኢትዮጵያ ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔዎች ያስፈልጋሉ ብላ የምታምን፤ ይሄንም ስትፈጽም የኖረች ሀገር ናት፤ በአፍሪካ ጉዳይ ማንም ጣልቃ መግባት የለበትም ትላለች፤ ለአፍሪካ አፍሪካውያን በቂ ናቸውና።
ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን በመሠረቱበት ጊዜ አፍሪካውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው መፍታት፣ የአፍሪካን መጻዒ ዕድል በራሳቸው መወሰን እንዳለባቸው ገልጸው ነበር።
በሪሁን ከበደ የአጼ ኃይለሥላሴ ታሪክ በተሰኘው መጽሐፋቸው ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሠረት የተናገሩትን ንግግር ሲጽፉ እኛ አፍሪካውያን ወዴት እንደምናመራ ማወቅ ይኖርብናል፤ ከየትስ እንደመጣን ማወቅ አለብን ወደፊት ለምናደርገው ሁሉ ያለፈውን ታሪካችንን ማወቅ ይገባናል ማለታቸውን መዝግበዋል።
በአፍሪካውያንነታችን ያለን ኩራት ታሪካችንን ማወቅ ይገባናል፤ በአፍሪካውያንነታችን ያለን ኩራት የሚገጥሙንን ችግሮች ሁሉ ለማስወገድ ትልቅ መሣሪያችን ነው። ይህች ዓለም በየጊዜው አይደለም የተሠራችው። አፍሪካም የተፈጠረችው ሌሎች በዚህች ዓለም ያሉት ክፍለ ዓለሞች በተፈጠሩበት ጊዜ ነው። አፍሪካውያኖችም ሌሎች ሕዝቦች ያላቸው ስጦታ እና ችሎታ እንደዚሁም ጉድለቶች አሏቸው።
ከብዙ ሺህ ዘመናት በፊት በአፍሪካ ውስጥ በሌላው ክፍለ ዓለም ካለው ያላነሰ ሥልጣኔ ተዘርግቶ እንደነበረ ታሪክ ይመሰክራል። በዚያን ጊዜ አፍሪካውያን ነጻ እና በምጣኔ ሃብትም ራሳቸውን የቻሉ ሕዝቦች ነበሩ። ኑሮአቸው እና ባሕላቸው የተውሶ ያልኾነ የራሳቸው ነበር ብለዋል።
አፍሪካ በሙሉ ነጻ እንድትኾን የገባነውን ቃል ኪዳን እንደገና ስናድስ ባለፈው ጊዜ በደረሰብን በደል ቂም መያዝ አይገባንም። የቅኝ ገዥዎች በጭቆና ያሥተዳድሩ በነበረበት ጊዜ የሠሩትን ሥራ ሁሉ ያለፈውን ወደ ጎን ትተን ለወደፊቱ እንድከም። ባለፉት ዘመናት ከበደሉን ጋር በሰላም እና በመግባባት ለመኖር እንሞክር። ጥላቻን እና ቂምን አንተው፤ ቂም በቀልን መሣሪያ አናድርግ፤ ሥራችን እና ቃላችን ከኛ ከአፍሪካውያን ክብር ጋር የተያያዘ ይሁን፤ ጥረታችን ሁሉ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር መተባበርን እና መረዳዳትን መፍጠር ይሁን ነበር ያሉት።
ዛሬ ተረጋግተን በሙሉ ዕምነት እና ድፍረት ስለወደፊት እናስባለን። ዛሬ የምናስበው ለነጻይቱ አፍሪካ ብቻ ሳይኾን ስለአፍሪካ አንድነት ነው። ስለዚህም በምናስብበት እና በምንሠራበት ጊዜ ያለፈው ታሪክ ትምህርት ሊኾነን ይችላል። በጎሣ፣ በሃይማኖት እና በባሕል መለያየት አንድነትን ለመፍጠር እንቅፋት ሊኾኑ እንደማይችሉ ብዙ ምሳሌዎች አሉ።
አንድነት ኀይል እንደኾነ እናውቃለን፤ መለያየት ግን ደካማነትን የሰው መሣሪያነትን እንደሚያስከትል እናውቃለን። በመካከላችን ሊኖሩ የሚችሉትን ጥቃቅን ልዩነት ወደጎን ትተን ሁላችንም ለሚያስተባብረን ስለ አፍሪካ እንድነት መድከም አለብን። እርስ በርሳችን መነታረክ ትርፉ የሌላ ሲሳይ መኾን ነው ነበር ያሉት።
ኢትዮጵያ ከጥንት እስከዛሬ የአፍሪካውያን አንድነት፣ ዕድገት፣ የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚያሳስባት ሀገር ናት። ለዚህም ነው በዚህ ዘመንም ለሚፈጠሩ አፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔዎች እያለች የምትከራከረው።
የዓባይ የውኃ ጉዳይ ከአፍሪካ ማዕቀፍ ሲወጣ ለአፍሪካ ችግሮች አፍካዊ መፍትሔዎች ብላ ወደ አፍሪካ መልሳለች። በአፍሪካ ውስጥ ግጭቶች ሲፈጠሩ ወደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ሌሎች ተቋማት ሊሄዱ ሲሉ ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔዎች እያለች መፍትሔ የዘየደች፤ የአፍሪካን ዲፕሎማሲ አፍሪካዊ ጥቅምን ባሰከበረ እና የአፍሪካን አንድነት በጠበቀ መልኩ እንዲቃኝ ያደረገች ሀገር ናት።
አፍሪካውያን ራሳቸውን እንዲያዩ፤ የውጭ ጣልቃ ገብነትን እንዲቃወሙ፤ ረጅም እጆችን እንዲከላከሉ መሠረት የጣለች፣ ፋና ወጊ ኾና የሠራች እና እየሠራች ያለች ናት።
አፍሪካ በራሷ ትኮራለች፤ በራሷ መፍትሔ ችግሮቿን ትፈታለች፤ መፍትሔ የምትሰጥ እንጂ መፍትሔ የምትቀበል አህጉር አለመኾኗን ለዓለም ታሳያለች።
#አሚኮ_ዜና #ዲፕሎማሲ #ኢትዮጵያ
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
