
ባሕር ዳር: ሰኔ 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ማንነት የሚከበረው እና አንገትን አቃንቶ መጓዝ የሚቻለው ሀገር በዓለም መድረክ ስሟ እና ሰንደቋ ከፍ ሲል ብቻ ነው። እርግጥ ነው ሀገራት ያሉበት ስታራቴጅያዊ አቀማመጥ ለተደማጭነታቸው ወሳኝ ጉዳይ ቢኾንም የዲፕሎማሲያቸው ጥንካሬም የማይተካ ሚና አለው።
በርካታ ሀገራት ከፍ ብለው የሚታዩት እና ጎልተው የወጡት ካላቸው ሀብት ጋር አዳምረው የዲፕሎማሲ ሥራቸውን ከፍ አድርገው ማየት በመጀመራቸው ነው፡፡ ታላላቅ የሚባሉ ሀገራት ከአሜሪካ እስከቻይና፤ ከቱርክ እስከፈረንሳይ እና ሩስይ ከአውሮፓ ሀገራት እስከ ኤሽያ እና መካከለኛው ምሥራቅ ያሉ ሀብታም ሀገራት ዛሬ ወደ ተስፈኛዋ ሀገር አፍሪካ ፊታቸውን ያዞሩት የዕድገታቸውን ምንጭ እና የወደፊቱን የአህጉሩን ተስፋ በመመልክት ነው፡፡
እነዚህ ሀብታም ሀገራት ዲፕሎማሲያቸውን ወደ አፍረካ ሲያደርጉ ቅድሚያ የሚመለከቷት ሀገር ኢትዮጵያን ነው፡፡ ለምን ይህ ኾነ ካሉ ሀገሪቱ በአፍረካ ቀንድ ያላት ስታቴጅካዊ ቦታን ጨምሮ የዲፕሎማሲዋ ከፍታ ልቆ ለመውጣቱ ዋና ምክንያት ኾኖ መቀመጡ አይቀሬ ነው፡፡
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ ዶክተር ፍሬው የኔዓለም ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ከቅኝ ግዛት ጀምሮ ጥብቅና በመቆም እና በዱፕሎማሲው መስክ ብቻዋን በመታገል ትታወቃለች ለዚህ ደግሞ ብልህ መሪዎቿ ትልቁን ቦታ ይይዛሉ፡፡
ዕውቀቱን እየዋጁ እና የአፍሪካንም ኾነ የዓለምን ችግሮች እየቃኙ የዲፕሎማሲ ሥራን የሚከውኑት ኢትዮጵያዊያን አሁንም ወቅቱን የሚዋጅ የዲፕሎማሲ ማስተሳሰሪያ ገመድን ይዘው ብቅ ብለዋል፡፡ ይህም የአረንጓዴ ልማት ዲፕሎማሲ ነው፡፡ ይህ የዲፕሎማሲ ሥራ ሁሉንም የዓለም ሀገራት የሚነካ በመኾኑ ጆራቸውን አንቅተው እና አንገታቸውን ቀና አድርገው የሚሰሙት እና የኢትዮጵያን ድምጽ ተገደው የሚያዳምጡት ጉዳይ ነው፡፡
አሁን ላይ ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ እየተናጡ፤ በጎርፍ እየተበሉ በንፋስ እየተወሰዱ እና በሀሩር እየነደዱ ያሉበት ጊዜ ነውና ኢትዮጵያ ይዛ ብቅ ስላለችው የአረንጓዴ አሻራ ዲፕሎማሲ ጀሮ መስጠታቸው አልቀረም፡፡ ከአፍረካ ሀገራት እስከ ዓለም ሀገራት ታላላቅ መድረኮች ኢትዮጵያ እየተገኘች እየተከሰተ ላለው ችግር ያገኘችውን እና እየተገበረች ስላለችው የአረንጓዴ ፖሊሲ በማስረዳት ላይ ናት፡፡
በአንድ ቀን የአረንጋዴ አሻራ የምትተክለው ችግኝ የመትከል ዘመቻ ደግሞ አፍ አውጥቶ በመላው ዓለም የዲፕሎማሲ ሥራ እየሠራም ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያ ለውጥ ከራስ ይጀምራል እንዲሉ ከራሷ በመነሳት ምሥራቅ አፍሪካን ያካለለ የአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ሥራ እየከወነችም ትገኛለች ይህም ቀጣናው ላይ የአረንጓዴ አሻራን በማስፋት እና በምሥራቅ አፍሪካ ለሌሎች የዓለም ሀገራት ማስተሳሰሪያ ገመድ እንዲኾን ማድረጉ አይቀሬ ነው፡፡
ሀገራት ድንበር ቢኖራቸውም የአየር ንብረት ለውጥ ግን ድንበር አልባ ነው እና ችግሩ ሲጠና ዲፕሎማሲው ወደ ኢትዮጵያ ቀስ በቀስ መትመሙ አይቀሬ ይኾናል፡። አሁንም ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ለሚመክረው ኮፓ 32 አዘጋጅ ኾና ስትመረጥ ምክንያቱ በአረንጓዴ ልማት የሠራችው ዲፕሎማሲ መኾኑ ገሀድ የወጣ እውነት ስለመኾኑ መምህሩ አብራርተዋል፡።
ብልህ መሪዎች የዘየዱት የአረንጓዴ አሻራ ዲፕሎማሲ ዛሬ ሀገሪቱ ቀና ብላ በዓለም መድረክ እንድትናገር እና እንድትከበር አስችሏል፡፡
ትኩረት ስጡኝ ብለህ ሳይኾን ለችግሮች መፍትሔ በማፍለቅ ትኩረትን መሳብ ብልጠት የተሞላበት ዲፕሎማሲ አካሄድ የሚኾነውም ለዚህ ነው፡፡ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ብቅ ያሉት የሕንድ፣ የፈረንሳይ፣የቱርክ፣ የጣሊያን እና ሌሎችም የአፍረካ እና የዓለም ሀገራት መሪዎች አረንጓዴ አሻራቸውን እያሳረፉ እና ለኢትዮጵያም ክብር እና ምስጋና እየቸሩ ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡
ይህም በሀገራት መካካል ያለውን የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ መጠራጠር በማስወገድ የጋራ ተጠቃሚነትን ከማሳደግ ባለፈ በአካባቢው ሰላምን ለማስፈን እና ችግሮችን በጋራ ለመታገል ሁነኛ መንገድ እንደኾ በገሀድ ታይቷል፡፡
#አሚኮ_ዜና #ዲፕሎማሲ_የአረንጓዴ_አሻራ #ኢትዮጵያ
በምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
