
ባሕር ዳር: ሰኔ 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን ከፍ በማድረግ በምሥራቅ አፍሪካ ቀንድ ተሰሚነቷን አጉልታለች። “ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ” በሚል ጠንካራ አቋሟ የምትታወቀው ኢትዮጵያ የዓለም መንግሥታትን ትኩረት እየሳበች ነው።
በ2018 ዓ.ም የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤን፣ ሁለተኛው የጣሊያን-አፍሪካ ጉባኤ፣ የምሥራቅ አፍሪካ ዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት ጉባኤ፣ ዓለም አቀፍ የሳይበር ደኅንነት እና የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (ኤአይ) ኮንፈረንስ እና ሌሎች ዓለማቀፋዊ ኹነቶችን በማስተናገድ እና በስኬት በማጠናቀቅ ዲፕሎማሲዎን ከፍ አድርጋለች።
የውጭ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ፣ የኢንቨስትመንት ዘርፏን ውጤታማ ለማድረግ፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ፣ በጎረቤት ሀገራት በምሥራቅ አፍሪካ ብሎም በአፍሪካ ደረጃ ግንኙነቶችን በማሳለጥ ለቀጣናው ሰላም እና ዕድገት እየሠራች ነው።
በ2018 ዓ.ም የቱርክ ፕሬዝዳንት ረጅብ ጠይፕ ኤርዶዋን፣ የእስራኤል ፕሬዝዳንት አይዛክ ሄርዞግ፣ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ፣ የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ፣ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዎ ጉተሬዝ እንዲሁም ሌሎች የዓለም እና የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በሁለትዮሽ ግንኙነት፣ በኢኮኖሚ እና በማኅበራዊ ልማት ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር መክረዋል።
ለአፍሪካ የነጻነት ምልክት የኾነችው ኢትዮጵያ ዘመኑ የሚፈልገውን የዲፕሎማሲ ግንኙነት በማሳለጥ የአፍሪካ መሪነቷን እያረጋገጠች ነው። በዚህ ዓመት በዲፕሎማሲያዊ ዘርፍም ውጤታማ መኾንም ተችሏል።
የኢትዮጵያ ተጽዕኖ ፈጣሪነት፣ የልማት ተነሳሽነት፣ ድህነት እና ኃላ ቀርነትን ለማስወገድ የምታከናውናቸው ተግባራት በርካታ የዓለም ሀገራት መሪዎች የሁለትዮሽ ግንኙነትን ለመፍጠር ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ አድርጓቸዋል።
ዘላቂ ተጠቃሚነትን እና ኢኮኖሚያዊ ልማትን ይበልጥ በማሳደግ በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ልማት ተወዳዳሪ ለመኾን መንግሥት በትኩረት እየሠራ መኾኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተለያዩ ጊዜያት ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ሰላማዊ ዲፕሎማሲ እና የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት አድርጋ የውጭ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን ለማሳደግ እየሠራችም ነው።
#አሚኮ_ዜና #ዲፕሎማሲያዊ_ግንኙነት #ኢትዮጵያ 🇪🇹
ዘጋቢ:-ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
