🇪🇹 “ከራሷ አልፋ ለሌሎች የኖረች፤ ለእውነት እና ለፍትሕ የቆመች”

7

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ነጻነቷን ለማስከበር ለዘመናት ከጠላቶቿ ጋር ተዋግታለች፤ በጀግንነት ጸንታ ሉዓላዊነቷን አስከብራለች፤ እንደ እሳት በሚፋጀው ክንዷ ቅኝ ገዢዎችን እያቃጠለች የነጻነት ክብሯን አስጠብቃለች፤ የትኛውም ሀገር የሌለውን የነጻነት ታሪክ በደማቁ ጽፋለች።

እርሷ ከራሷ አልፋ ለሌሎች ነጻነት ተዋግታለች፤ ደምታለች፤ ልጆቿን ገብራለች፤ አፍሪካውያን ነጻነታቸውን እንዲያገኙ፤ ጥቅማቸውን እንዲያስከብሩ መሪ እና ሠብሣቢ እናት ኾና ኖራለች፤ ፍትሕ ወደ አንድ በኩል ባዘነበለበት ዘመን ለፍትሕ እና ለዕውነት ቆማለች። ይህን አቋሟም ለዘመናት አጽንታለች።

ኢትዮጵያ በታሪኳ ከማንም ጥቅም ላይ ቆማ አታውቅም። በጥቅሟ ላይ የሚቆሙባትንም አትታገስም። በረጅም ታሪኳ የሌሎችን ሀገራት ብሔራዊ ጥቅም ያልነካች፤ በሌሎች ብሔራዊ ጥቅሞች ላይ አሉታዊ ተግባር ያልፈጸመች፤ ሌሎችም እንዲፈጽሙ ይሁንታ ያልሰጠች ለጎረቤት እና ለወዳጅነት ቅድሚያ የምትሰጥ ሀገር ናት።

ኢትዮጵያ በታሪኳ የሌሎችን ጥቅም የመውሰድ ፍላጎት እና ምኞት ቢኖራት ማድረግ የሚያስችል አቅም ነበራት። እርሷ ግን ለዘላቂ ወዳጅነት እና ጥቅም ስትል ይሄን ማድረግ አልፈለገችም።

ጳውሎስ ኞኞ የኢትዮጵያ እና የኢጣሊያ ጦርነት በተሰኘው መጽሐፋቸው ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ ለዘመናት የተደጋገመ ሙከራ ተደርጓል። ኢትዮጵያውያን ግን ሀገራቸውን በሌላ ባዕድ ሳያሲዙ ባላቸው ኀይል ሲከላከሉ ቆይተዋል። በአውሮፓም ኾነ በኢሲያ በአፍሪካም የሚነሱ ታላላቅ መንግሥታት ጉልበት አያገኙ ግዛታቸውን በሚያሰፉበት ጊዜ ኢትዮጵያንም ለመደረብ ብዙ ጊዜ ሞክረዋል። ኢትዮጵያውያን ግን ለማንም ሳይበገሩ እና ሳይገብሩ እስካሁን ሀገራችንን አስከብረው ቆይተዋል ይላሉ።

ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን የማይለቁ እና የሌላ ሀገር የማይፈልጉ በመኾናቸው እንጂ እንደ ታሪክ ፀሐፊዎች መስካሪነት ከኾነ አውሮፓንም ኾነ እስያን እያለፉ የሚይዙበት ብዙ ዘመን ነበር። ነገር ግን ይሄን አይፈልጉትም ብለው ጽፈዋል።

ኢትዮጵያ የራሷን ነጻነት የጠበቀች፤ ሉዓላዊነቷን ያስከበረች ገናና ታሪክ ያላት ሀገር ናት። በቅኝ ገዢዎች ነጻነታቸውን የተነጠቁ አፍሪካውያን እና መላው ጥቁር ሕዝብ ነጻነቱን እንዲያገኝ የታገለች፤ ያታገለች፤ መውጫ መንገዱን ያሳየች፤ ከራሷ አልፋ ለሌሎች የኖረች ሀገር ናት።

ኢትዮጵያ ጂኦፖለቲካዊ ስትራቴጂን በአግባቡ የተረዳች፤ በጂኦ ፖለቲካው የራሷን ጥቅም የሌሎችን ጥቅም በማይነካ መልኩ ለማስከበር እየሠራች የመጣች እና እየሠራች ያለች ሀገር ናት።

ፕሮፌሰር ላጲሶ ጌ ዴሌቦ የኢትዮጵያ ረጅም የሕዝብ እና የመንግሥት ታሪክ በተሰኘው መጽሐፋቸው ጂኦፖለቲካ የአንድ አካባቢ ወይም ሀገር የስትራቴጂ፣ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ሁኔታዎች መስተጋብር እና መገለጫ ነው ይላሉ። የኢትዮጵያ ሕዝብ መንግሥት እና ሕዝብ ብሔራዊ ሕልውና፣ ሕይወት እና ነጻነት ከቀይ ባሕር እና ከዓባይ ሸለቆ ጂኦፖለቲካ ጋር በቅርብ እና በጥብቅ የተያያዘ ነው ይላሉ።

ጂኦፖለቲካ በአንድ ሀገር ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ እንደ አካባቢው እና እንደ ዘመኑ ተጨባጭ ሁኔታ መሠረታዊ የዕድገት አስተዋጽኦ ሊያደርግ ወይም አፍራሽ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችል የጅኦግራፊ፣ የእስትራቴጂ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ሁኔታዎች መግለጫ ነው ይሉታል።

ኢትዮጵያም ይሄን በአግባቡ ተረድታ የምትሠራ ሀገር ናት። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በጥር 2018 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በሰጡት ማብራሪያ የአፍሪካ ቀንድ እንዳይቀደድ የተሰፋ፣ እንዳይጣመር የተቀፈደደ ጆፖለቲክስ ያለበት ነው ብለዋል።

እንዳንለያይ እዚህም እዚያም አንድ አይነት ባሕል፣ ቋንቋ፣ ዘር አለ፤ በጣም የተሳሰረ ነው ይላሉ። የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ፉክክር ያለበት መኾኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደ አፍሪካ ቀንድ በባሕል፣ በቋንቋ እና በበብዙ ሃብቶች የተሳሰረ አካበቢ የለም ብለዋል። ይሄን ተጠቅሞ መልማት ይቻላል፤ ነገር ግን የሁለቱ ውኃዎች ጉዳይ ቀንዱን እያተረማመሰ፤ በእኛ ጉዳይ የሚገቡ ኀይሎችንም እያሰፋ በመሄዱ አንደኛው ጎረቤት ለሌላው ጋሻ መኾን ሲገባው ጥይት አቀባይ ኾኖ ቀረ፤ አንደኛው ለሌላኛው መከታ መኾን ሲገባው አንደኛው ለሌላኛው ችግር አስተላላፊ ኾነ ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ ችግርን ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት እያደረገች መኾኗን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል የምታምን፤ የሌሎችን ጥቅም የማትነካ፤ የሌሎችን ጥቅም በማክበር የራሷንም ጥቅም ለማስከበር የምትሠራ ሀገር ናት።

ለጋራ ጥቅም እና ለጋራ ዕድገት ኢትዮጵያም ታግዛለች፤ እነርሱም ማገዝ አለባቸው ነው የሚሉት። የኢትዮጵያ አቋም በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ዲፕሎማሲን ማራመድ ነው፤ አፍሪካውያን ከኢትዮጵያ የሚፈልጉት ካለ ክብሯን እና ጥቅሟን ባከበረ መልኩ በሰጥቶ መቀበል መርሕ መጠየቅ ይችላሉ የሚል የጸና አቋም አላት። ነገር ግን ጠያቂዎች ብቻ ሳይኾኑ ሌሎችም ኢትዮጵያ የምትፈልገውን መስጠት አለባቸው።

ከራሷ አልፎ ለሌሎች ሀገራት የምትቆመው ኢትዮጵያ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ታሪኮች አሏት፤ አሁን ታላላቅ ስኬቶችን እያስመዘገበችም ነው።

#አሚኮ_ዜና #ዲፕሎማሲ #ኢትዮጵያ 🇪🇹

በታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የዳኝነት እና የጋዜጠኝነት የሙያ ሥነ ምግባርን መሠረት በማድረግ ለአንድ ዓላማ መሥራት ይገባል” አቶ ዓለምአንተ አግደው
Next articleየኢትዮጵያ 🇪🇹 አዲስ የዲፕሎማሲ ምዕራፍ ከቀጣናዊ ተፅዕኖ እስከ ዓለም አቀፍ ትኩረት