“የዳኝነት እና የጋዜጠኝነት የሙያ ሥነ ምግባርን መሠረት በማድረግ ለአንድ ዓላማ መሥራት ይገባል” አቶ ዓለምአንተ አግደው

5

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ​የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፍርድ ቤቶች የለውጥ ሥራዎች እና በፍርድ ቤት ጉዳዮች አዘጋገብ ዙሪያ ለሴት ጋዜጠኞች በባሕር ዳር ሥልጠና እየሰጠ ነው።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው እንደገለጹት ፍርድ ቤቶች በሕገ መንግሥት የዳኝነት አገልግሎት እንዲሰጡ የተቋቋሙ ሦሥተኛ የመንግሥት አካላት ናቸው።

በሕገ መንግሥቱ በተሰጣቸው ሥልጣን መሠረትም የፍርድ ቤቶች ሚና ሕግን እና ማስረጃን መሰረት አድርገው ገለልተኛ ፍትሕ መስጠት ነው ብለዋል።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትም የዜጎችን ፍትሕ የማግኘት መብት ለማረጋገጥ የፍትሕ ተደራሽነትን ማረጋገጥ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ሥለመኾኑም አብራርተዋል።

የዲጂታላይዜሽን አሠራርን ተግባራዊ በማድረግ ቀልጣፋ የፍትሕ ሥርዓትን ውጤታማ በኾነ መንገድ እየዘረጋ አጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።

የሕግ እና ፍትሕ ኢንስቲትዩትን በማደራጀት የዳኞችን እና የፍትሕ ባለሙያዎችን አቅም ለመገንባት እየተሠራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

የባሕል ፍርድ ቤቶችን በቀበሌ ደረጃ በማደራጀት ሥራ እየተሠራ ይገኛል ነው ያሉት። የተከላካይ ጠበቆች ጽሕፈት ቤት መደራጀቱንም አንስተዋል።

በንግድ እና ኢንቨስትመንት የሚነሱ ክርክሮችን በአጭር ጊዜ ለመፈታት የሚያስችል የግልግል ዳኝነት ማዕከል ለማቋቋም ሰፊ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

የመገናኛ ብዙኅንም የዜጎችን መረጃ የማግኘት መብት መሠረት አድርገው ዜጎችን በማንቃት በሀገራቸው ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲኾኑ በማድረግ የማይተካ ሚና እንዳላቸው ነው የገለጹት።

ሁለቱም ተቋማት በአንድ ሀገር የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ የሕግ የበላይነት መረጋገጥ፣ ለማኅበራዊ እና ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ተቋማት ስለመኾናቸውም አስረድተዋል።

የዳኝነት እና የጋዜጠኝነት የሙያ ሥነ ምግባርን መሠረት በማድረግ በቀጣይነት ተቀራርቦ ለአንድ ዓላማ መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

#አሚኮ_ዜና #ፍርድ_ቤቶችና_ጋዜጠኝነት #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ 🇪🇹

ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article🇪🇹 የዓለም ቁንጮ ቢሊየነሮችን የሳበው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ
Next article🇪🇹 “ከራሷ አልፋ ለሌሎች የኖረች፤ ለእውነት እና ለፍትሕ የቆመች”