🇪🇹 የዓለም ቁንጮ ቢሊየነሮችን የሳበው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ

8

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ​ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት እየተከተለችው ያለው ንቁ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ፣ ሀገሪቱን የዓለም አቀፍ ባለሀብቶች እና የልማት አጋሮች ማዕከል እያደረጋት ይገኛል። በተለይም ለኢንቨስትመንት ያሳየችው ቁርጠኝነት እና እየተከናወኑ ያሉ የፖሊሲ ማሻሻያዎች፣ የዓለምን ኢኮኖሚ አቅጣጫ የሚወስኑ ቁንጮ ቢሊየነሮችን ቀልብ በመሳብ ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ አድርጓቸዋል።

ከእነዚህ መካከል አፍሪካዊው ስመ ጥር ባለሃብት አሊኮ ዳንጎቴ እና ዓለም አቀፉ በጎ አድራጊ ቢል ጌትስ የሚጠቀሱ ሲኾን፣ የየራሳቸው የኢንቨስትመንት እና የልማት አሻራዎችም በኢትዮጵያ ላይ እያሳረፉ ነው።

​በተለይም ናይጀሪያዊው አሊኮ ዳንጎቴ ኢትዮጵያ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በመቀጠል ልታሳካው አጥብቃ ትመኘው የነበረውን የማዳበሪያ ፋብሪካ ተስፋ ይዞ ብቅ ያለ ኾኗል። ይህም የኢትዮጵያን የኢኮኖሚው ዘርፍ ዲፕሎማሲ ፍሬ በተግባር የገለጠ ኾኗል።

የዳንጎቴ ግሩፕ ሊቀመንበር አሊኮ ዳንጎቴ ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርጉት ተደጋጋሚ ጉዞ ከኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አቅም ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው። በተለይም በኢትዮጵያ እየተገነባ ያለው ግዙፍ የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የኢትዮጵያን የግብርና ምርታማነት በአዲስ መልክ የሚቀይር ስትራቴጂካዊ ፕሮጀክት ነው።

ይህ ፋብሪካ ለአርሶ አደሮች የሚደርሰውን የአፈር ማዳበሪያ እጥረት ከመቅረፍ ባለፈ ሀገሪቱን የግብርና ምርቶች ማዕከል እንድትኾን ያስችላታል። የፕሮጀክቱ መጀመር ኢትዮጵያ በጠነከረ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲዋ የውጭ ባለሃብቶችን መሳብ እንደምትችል እና የቀጣይ ዕድገቷን ለማረጋገጥ በወሳኝ ምእራፍ ላይ ለመገኘቷ ማሳያም ነው።

ለኢንዱስትሪ መሠረተ ልማት ያላትን ምቹነት እና ለግሉ ዘርፍ የምትሰጠውን ትኩረት ለዓለም የመሰከረም ነው።
​ሌላው የዓለም ቁንጮው ባለሀብት እና በጎ አድራጊ ቢል ጌትስም ወደ ኢትዮጵያ የተሳቡ እና ከአንድም ሁለቴ አዲስ አበባን የረገጡ፣ ወደገጠሩም ወጥተው በኢትዮጵያ የስንዴ ማሳዎች ላይ የተመላለሱ ስመ ጥር ሰው ናቸው።

ባለሀብቱ ቢል ጌትስ የሚያደርጉት ጉብኝት፣ በዋናነት በዘላቂ ልማት እና በሰው ኀይል ልማት ላይ ያጠነጠነ ነው። ቢል ጌትስ በተለይም በግብርና ምርታማነት፣ በጤናው ዘርፍ እና በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር በአጋርነት የሚሠሩ ኾነዋል።

የእነዚህ ግዙፍ ባለሀብቶች መምጣት በዘፈቀደ የሚከናወን ሳይኾን፣ ውጤታማ በኾነ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የመጣ ነው።

እንደ ዳንጎቴ እና ቢልጌትስ ያሉ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸው ኢትዮጵያ ደህንነቷ የተጠበቀ እና ለኢንቨስትመንት ምቹ መኾኗን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ዋነኛ ጠቋሚ ነው። በዚሁ በጀት ዓመት በተካሄደው በኢንቨስት ኢን ኢትዮጵያ 2026 ፎረም፤ ከቻይና፣ ፖላንድ፣ ሕንድ፣ ሲንጋፖር እና ኬንያ ከመጡ አጋሮች ጋር የ13 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ታሪካዊ የኢንቨስትመንት ስምምነት መፈረሙም አይዘነጋም።

ይህ ድባብ ሌሎች ታናናሽ እና መካከለኛ ኢንቨስተሮችንም ወደ ኢትዮጵያ በመሳብ የሥራ ዕድል መፍጠር እና የውጭ ምንዛሬን ለማግኘት የሚያስችል በር ይከፍታል።

#አሚኮ_ዜና #ዲፕሎማሲ #ኢትዮጵያ 🇪🇹

በአሚናዳብ አራጋው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article🇪🇹የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ለቱሪዝም ከፍታ!
Next article“የዳኝነት እና የጋዜጠኝነት የሙያ ሥነ ምግባርን መሠረት በማድረግ ለአንድ ዓላማ መሥራት ይገባል” አቶ ዓለምአንተ አግደው