🇪🇹የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ለቱሪዝም ከፍታ!

4

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ)የበርካታ ቅርስ ባለቤት የኾነችው ኢትዮጵያ የቱሪዝም ኢኮኖሚ ዘርፏን ለማሳደግ የተለያዩ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን አከናውናለች።

የኢትዮጵያ የቱሪዝም ልማት ዲፕሎማሲ ሀገሪቱ ያላትን እምቅ ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ ጸጋዎችን በመጠቀም ዓለም አቀፍ ገጽታዋን ለመገንባት፣ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እና የኢኮኖሚ ዕድገቷን ለማፋጠን ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እያከናወነች ነው።

መንግሥት በ2018 ዓ.ም ታዋቂ የማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎችን፣ ከፍተኛ የውጭ ሀገራት አምባሳደሮችን በመቀበል በቱሪዝም ዘርፍ የሀገርን ገጽታ መገንባት ችሏል።

ከታዋቂ ማኅበራዊ አንቂዎች መካከል ከ50 ሚሊዮን ተከታዮች በላይ ያሉት ታዋቂው አሜሪካዊ ዩቲዩበር አይሾው ስፒድ በኢትዮጵያ ቆይታው “ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከሚገኙ ትላልቅ እና አስደናቂ ሀገራት አንዷ ናት” ሲል ዕድገቷን አሞካሽቷል። በኢትዮጵያ ስላለው የመሠረተ ልማት ግንባታ መደነቁንም ተናግሯል።

የዓድዋ ሙዚየምን በባዶ እግሩ በመጎብኘት ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ነጻነት የከፈለችውን ታሪክ በቀጥታ ስርጭቱ አጋርቷል።

ሌላኛው ከ19 ሚሊዮን በላይ ተከታይ ያሉት በዓለም አቀፍ ደረጃ በዜና እና ወቅታዊ መረጃ አቀራረቡ የሚታወቀው እንግሊዛዊ የማኅበራዊ አንቂ ዲላን ፔጅ በኢትዮጵያ የሚገኙ ታሪካዊ የቅርስ ቦታዎችን፣ ባሕላዊ እሴቶችን በመጎብኘት ለዓለም አስተዋውቋል።

በቅርቡም የአፍሪካ ተጽዕኖ ፈጣሪ ወጣቶች በአዲስ አበባ በመገኘት የኢትዮጵያን የቱሪዝም፣ የመሠረተ ልማት እና የዲጅታል ዕድገትን ተመልክተዋል።

ከማኅበራዊ አንቂዎች ባሻገር የበርካታ ሀገራት መሪዎች፣ አምባሳደሮች እና የውጭ ጎብኝዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ በመጋበዝ መንግሥት🏔 የቱሪዝም ዲፕሎማሲ ልማትን ውጤታማ ማድረግ ችሏል።

የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የኢትዮጵያን ቱሪዝም መዳረሻ በማስተዋወቅ ረገድ ውጤታማ ተሳትፎ መደረጉን በተቋሙ በዘጠኝ ወር አፈጻጸም ወቅት ገልጸዋል። በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ800 በላይ የመስህብ ሀብቶች የተለዩበት ስኬታማ ወቅት እንደነበርም ተናግረዋል፡፡

የቱሪዝም ሚኒስቴር ከተለያዩ ሀገራት ጋር ስምምነትን በማድረግ በቱሪዝም ልማት፣ በቅርስ ልማት እና ጥበቃ ረገድ የልምድ ልውውጥ በማድረግ በጋራ ለመሥራት በርካታ ተግባሮች ተከናውነዋል።

🌄የቱሪዝም ልማትን በማፋጠን ከዘርፉ የሚገኝ ገቢን በማሳደግ የኢኮኖሚ አቅምን ከፍ ለማድረግ መንግሥት በትኩረት እየሠራ ይገኛል።

የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማት፣ የቅርስ ጥገና እና እንክብካቤ በማድረግ፣ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በመገንባት፣ የዲፕሎማሲ ግንኙነትን በማጠናከር መንግሥት በትኩረት እየሠራም ነው።

#አሚኮ_ዜና #የቱሪዝም_ዲፕሎማሲ #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ 🇪🇹

ዘጋቢ:-ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሰላም ጥረቱ በክልሉ የተሻለ የትራንስፖርት እና የንግድ እንቅስቃሴ እንዲኖር አስችሏል” እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር)
Next article🇪🇹 የዓለም ቁንጮ ቢሊየነሮችን የሳበው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ