
ባሕር ዳር: ሰኔ 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ)ባለፉት ጊዜያት በአማራ ክልል ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር በሰዎች የዕለት ተዕለት ሕይወት ላይ ጥሎት የነበረው ጠባሳ ቀላል አልነበረም። ይህም ማኅበረሰቡ ለከፋ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ቀውስ ተዳርጎ መቆየቱን የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር) ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ አስታውሰዋል።
ኾኖም ግን ያ አስከፊ ወቅት አልፎ አሁን ላይ በሕዝቡ እና በጸጥታ መዋቅሩ የተቀናጀ ጥረት የክልሉ ሰላም ወደ ቀደመ ጤናማ እንቅስቃሴው እየተመለሰ መኾኑን ይናገራሉ።
ዛሬ በክልሉ ለሚታየው አንጻራዊ መረጋጋት ዋነኛው ባለቤት ራሱ ማኅበረሰቡ እንደኾነ ኀላፊው ገልጸዋል።
ሕዝቡ ሰላምን ለማስፈን ከጸጥታ መዋቅሩ ጎን በመቆም አመርቂ ተግባራት እያከናወነ ይገኛልም ብለዋል። በተለይም የሚያጠራጥሩ የጸጥታ ስጋቶችን በንቃት በመጠቆም የከተማ ሰላምን አስተማማኝ እያደረገ ነው።
የትጥቅ ትግልን መፍትሔ አድርገው ወደ ጫካ የገቡ ታጣቂዎችን በመምከር እና በመገሰጽ በርካቶች የሰላም አማራጭን ተቀብለው ወደ ቀያቸው እና ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እንዲመለሱ ተደርጓል።
ኅብረተሰቡ የጽንፈኝነትን ተግባር በሰልፍ ወጥቶ በይፋ ከመቃወም ባለፈ ለጸጥታ መዋቅሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እና እገዛ በግንባር ቀደምትነት እያበረከተም ይገኛል።
በዚህ የጋራ ርብርብ ምክንያት አሁን ላይ በክልሉ ከበፊቱ የተሻለ አንጻራዊ ሰላም ሰፍኗል። ይህ መረጋጋት ደግሞ በሰዎች የኑሮ ሂደት ላይ ትልቅ ለውጥ እያመጣ ነው፤ የሰላም ጥረቱ በክልሉ የተሻለ የትራንስፖርት እና የንግድ እንቅስቃሴ እንዲኖር አስችሏል ነው ያሉት ቢሮ ኀላፊው።
በተለይም “ወሳኝ የንግድ መስመሮች እየተከፈቱ ነው፤ የትራንስፖርት እና የንግድ እንቅስቃሴውም መልሶ እያንሰራራ ይገኛል፤ ሕዝቡ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ የመሥራት እና የመኖር ዕድሉ ከበፊቱ እጅግ የተሻለ ኾኗል” ነው ያሉት ዶክተር እሸቱ የሱፍ
መንግሥት አሁንም ቢኾን የሰላም እጁን እንደዘረጋ መኾኑን ዶክተር እሸቱ አረጋግጠዋል። “ማንኛውም ጥያቄ አለን የሚሉ ታጣቂ ኀይሎች ጥያቄያቸውን በሠለጠነ መንገድ፣ በውይይት እና በምክክር መፍታት አለባቸው” ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
አሁን በክልሉ የተገኘው አንጻራዊ ሰላም እና መረጋጋት ዘላቂ እና የማይቀለበስ እንዲኾን የኅብረተሰቡ እና የጸጥታ መዋቅሩ እጅ እና ጓንት ኾኖ የመቀጠሉ ጉዳይ ወሳኝ እና አማራጭ የሌለው መኾኑም ተጠቁሟል።
#አሚኮ_ዜና #ወደሰላም_የተመለሱ_ታጣቂዎች_በልማት_ሥራ_ማሰማራት #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
