
ባሕር ዳር: ሰኔ 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አሜሪካና ኢራን ወታደራዊ ግጭቶችን ለማስቆም፣ የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመክፈትና በ60 ቀናት ውስጥ ዘላቂ የመፍትሄ ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚያስችል የ14 ነጥብ ጊዜያዊ የመግባቢያ ሰነድ ይፋ አድርገዋል።
“በአሜሪካ ዩናይትድ ስቴትስ እና በኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ መካከል የተደረገ የኢስላማባድ የመግባቢያ ሰነድ” በሚል የተነበበው ባለ 14 ነጥብ ረቂቅ ምን ይዟል?
👉 የተፋላሚዎቹ ሀገራት አጋሮች በሊባኖስም ሆነ በሁሉም ግንባሮች ጦርነትና ወታደራዊ ጥቃቶችን በአስቸኳይና በቋሚነት ለማቆም፣ ዳግም ጥቃት ላለመሰንዘር፣ እንዲሁም የሊባኖስን ሉዓላዊነት ለማክበር የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል።
👉 ሁለቱ ሀገራት የሌላኛውን ወገን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለማክበር፣ እርስ በእርስ በውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ ከመግባት ለመቆጠብ ቃል ይገባሉ።
👉 በጋራ ስምምነት ሊራዘም በሚችል ቢበዛ በ60 ቀናት ውስጥ ለመደራደርና የመጨረሻውን ስምምነት ለማሳካት ቁርጠኝነታቸውን ይገልጻሉ።
👉 አሜሪካ ስምምነቱ በተፈረመ በ30 ቀናት ውስጥ በኢራን ላይ የጣለችውን የባሕር ላይ ከበባ ሙሉ በሙሉ ለማንሳትና የመጨረሻው ስምምነት ሲደረስ ጦሯን ከኢራን አቅራቢያ ለማስወጣት ቃል ትገባለች።
👉 ኢራን ለንግድ መርከቦች ለ60 ቀናት ነፃና ደህንነቱ የተጠበቀ የባሕር ላይ ጉዞ በማመቻቸት፣ ፈንጂዎችንና እንቅፋቶችን በማስወገድ በ30 ቀናት ውስጥ እንቅስቃሴውን ወደነበረበት ትመልሳለች፤ ስለ ሆርሙዝ ወሽመጥ የወደፊት አስተዳደር ከኦማንና አጎራባች ሀገራት ጋር ትመክራለች።
👉 አሜሪካ ለኢራን መልሶ ግንባታና የኢኮኖሚ ልማት የሚውል 300 ቢሊዮን ዶላር ከቀጠናው አጋሮች ጋር ለማዘጋጀትና አስፈላጊ የሆኑ የፋይናንስ ፈቃዶችን በመስጠት አተገባበሩን በ60 ቀናት ውስጥ አጠናቃ ተግባራዊ ለማድረግ ቃል ገብታለች።
👉 አሜሪካ በኢራን ላይ የተጣሉትን ሁሉንም አይነት ማዕቀቦች (የተመድን እና የራሷን ጨምሮ) በተስማሙበት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ሙሉ በሙሉ ለማንሳት ቃል ስትገባ፤ ሁለቱም ሀገራት ይህንን ጉዳይ በድርድሩ ቅድሚያ ሰጥተው በአስቸኳይ ለመፍታት ተስማምተዋል።
👉 ኢራን የኑክሌር መሳሪያ ላለማምረት በድጋሚ ስታረጋግጥ፤ ሁለቱ ሀገራት የተከማቸውን የበለጸገ የኑክሌር ማዕድን በዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ቁጥጥር ስር ለማቅለጥና ስለወደፊቱ የኢራን የኑክሌር ማበልጸግ ፍላጎቶች ዙሪያ በጋራ ለመወያየት ተስማምተዋል።
👉 የመጨረሻው ስምምነት እስኪደረስ ድረስ ሁለቱም ሀገራት ነባራዊ ሁኔታቸውን ለመጠበቅ ተስማምተዋል፤ በዚህም ኢራን የኑክሌር ፕሮግራሟን አሁን ባለበት የምታቆይ ሲሆን፣ አሜሪካ ደግሞ አዲስ ማዕቀብ ላለመጣልና በቀጠናው ተጨማሪ ጦር ላለማሰማራት ተስማምታለች።
👉 አሜሪካ ማዕቀቦቹ ሙሉ በሙሉ እስኪነሱ ድረስ፤ ለኢራን የነዳጅ ምርቶች ኤክስፖርት እንዲሁም ለተያያዥ የባንክ፣ የኢንሹራንስና የትራንስፖርት አገልግሎቶች ከቅጣት ነፃ የሚያደርጉ ፈቃዶችን ለመስጠት ቃል ትገባለች።
👉 አሜሪካ የታገዱ የኢራን ገንዘቦችና ንብረቶች ሙሉ በሙሉ ተለቅቀው በኢራን ማዕከላዊ ባንክ አማካኝነት ለተፈለገው አገልግሎት (ክፍያ) እንዲውሉ አስፈላጊውን ፈቃድ ሁሉ ለመስጠት ቃል ገብታለች።
👉 አሜሪካና ኢራን የስምምነቱን አፈፃፀምና የቀጣይነት ተገዢነት የሚከታተል አስፈፃሚ አካል (አሠራር) ለማቋቋም ተስማምተዋል።
👉 አንቀጽ 1፣ 4፣ 5፣ 10 እና 11 በተግባር ላይ መዋል ሲጀምሩ፤ አሜሪካና ኢራን በቀሪዎቹ አንቀጾች ላይ ብቻ በማተኮር የመጨረሻውን ስምምነት ድርድር ይጀምራሉ።
👉 የመጨረሻው ስምምነት አስገዳጅ በኾነ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ ይጸድቃል።
በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
