ኢትዮጵያ ከመጀመሪያው ጀምሮ የጣና ፎረምን ዋና ባለቤት ኾና እያስተናገደች ቀጥላለች።

20
ኢትዮጵያ በርካታ አሕጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ኮንፈረንሶችን የማስተናገድ የቆየ ታሪክ አላት። አፍሪካውያንን አሥተባብራ በማንቃት፣ አህጉራዊ እና ቀጣናዊ ድርጅቶች እንዲመሠርቱ እና በአፍሪካ ችግሮች ዙሪያ እንዲመክሩ የማድረግ የቆየ ልምድ አላት።
የዚሁ አካል የኾነው የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት እንዲመሠረት ከማድረግ ጀምሮ የድርጅቱ መቀመጫ እስከመኾን ደርሳለች። በርካታ የዓለም ዓቀፍ እና አህጉራዊ ኮንፈረንሶችንም እያስተናገደች ትገኛለች። የአፍሪካውያን የመወያያ እና የመፍትሔ ምንጭ የኾነው የጣና ፎረምን እያስተናገደችም ዘልቃለች።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ዘሪሁን አበበ እንደተናገሩት የጣና ፎረም ሲመሠረት ዓላማውም የአፍሪካ መሪዎች በአህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተው ሃሳቦችን እንዲያንሸራሽሩ እና መፍትሔዎችን እንዲያመነጩ ያለመ ስለመኾኑ ያብራራሉ።
ፎረሙ አፍሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን እንቅስቃሴ የምትመለከትበት ነው ብለዋል። በአሕጉሪቱ የሚስተዋሉትን ችግሮች፣ የሰላም እና ደኅንነት አጀንዳዎች በአግባቡ ተመልክታ በራሷ ለመፍታት የምትመክርበት መድረክ ስለመኾኑም አብራርተዋል።
የአፍሪካን አጀንዳዎች ለዓለም ማስተዋወቅም የፎረሙ ሌላኛው ግብ ስለመኾኑ ጠቁመዋል። አፍሪካ ራሷን ከዓለም ጋር የምታይበት እና ፍላጎቷን ፈትሻ የምታሳይበት ስለመኾኑም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከመጀመሪያው ጀምሮ የጣና ፎረም መድረክ ዋና ባለቤት ኾና እያስተናገደች ቀጥላለች ነው ያሉት። በዚህ ሂደት ውስጥ ከፍተኛ አህጉራዊ ጠቀሜታ ያለውን የጣና ፎረምን አስተናጋጅ በመኾን አጋርነቷን እና መሪነቷን ያሳየችበት ነው ብለዋል።
የጣና ፈርጧ ባሕር ዳር ከተማም የፎረሙ ተሳታፊዎችን እየተቀበለች በማስተናገድ ትታወቃለች። ላለፉት 11 ዓመታት በተካሄዱት የፎረሙ መድረኮችም ይህንን ኀላፊነቷን በብቃት ተወጥታለች። ዘንድሮ ለሚካሄደው ለ12ኛው የጣና ፎረም መድረክም ዝግጅቷን አጠናቅቃ እንግዶቿን በመጠባበቅ ላይ ትገኛለች።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleበወገራ ወረዳ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የቆዩ ቡድኖች ወደ ሰላም ተመለሱ።