
ባሕር ዳር: ሰኔ 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በወቅታዊ የሰላም፣ የጸጥታ እና የቀጣይ የልማት ሥራዎችን በተመለከተ ከመንግሥት ሠራተኞች ጋር ውይይት አካሂዷል።
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የታየው አስደናቂ የአንድነት እና የትብብር መንፈስ ለልማት ሊውል እንደሚገባ በዕለቱ ተነስቷል።
የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ጊዜው ታከለ በምርጫው ወቅት የታየውን የትብብር መንፈስ ወደ ሰላም እና መልካም አሥተዳደር ሥራዎች ማሸጋገር እንደሚገባ ተናግረዋል።
የመንግሥት ሠራተኞች እና መሪዎች ሕዝቡ የጣለባቸውን አደራ ለማሳካት በትጋት እና በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስም የተጠናከረ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል። ለዚህም ለ18 ዓመታት ሳይፈታ የቆየው የስታዲየም ተነሺ ነዋሪዎች የካሳ ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱንም በማሳያነት አንስተዋል። ሌሎች የቆዩ የመልካም አሥተዳደር ችግሮች ትኩረት ተሰጥቶባቸው ምላሽ ያገኛሉ ነው ያሉት።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ሰብለ ዘውዱ የመንግሥት ሠራተኞች የሥራ ሰዓትን በማክበር የመልካም አሥተዳደር ክፍተቶችን ሊያስወግዱ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ሕዝቡም ከግል ይልቅ የጋራ ጥቅምን በማስቀደም ከመንግሥት ጋር ሊተባበር ይገባል ብለዋል።
በውይይት መድረኩ የተገኙ የመንግሥት ሠራተኞችም በከተማዋ ለሚከናወኑ የሰላም፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች መሳካት የበኩላቸውን ለመወጣት ቁርጠኛ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
