የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ትንሳኤ ማብሰሪያ እየኾነ መጥቷል።

6
ባሕር ዳር: ሰኔ 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ የኢትዮጵያ አዲስ ተስፋ እና ብርሃን ማሳያ የኾነውን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር፤ ተራ ዛፍ የመትከል ተግባር ሳይኾን የሀገርን ሁለንተናዊ ትንሳኤ የሚያበስር ታላቅ ብሔራዊ ንቅናቄ እና የይቻላል መንፈስ መገለጫ መኾኑን ገልጿል ።
ኢትዮጵያ ለዘመናት የገጠሟትን ዘርፈ ብዙ ፈተናዎች ተቋቁማ እንድትሻገር የሚያግዘው ይህ ንቅናቄ ባለፉት ዘመናት በአየር ንብረት መዛባት እና በደኖች መመናመን ምክንያት ለድርቅ እና ለአፈር መሸርሸር ተጋልጣ የነበረችው ምድሪቱ ዳግም እንድታገግም እያደረገ ይገኛል ብሏል።
በየዓመቱ የሚተከሉት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች የአየር ንብረት መዛባትን ለመከላከል እና የከርሰ ምድር ውኃን ለማበልጸግ ትልቅ አቅም መኾናቸው የተገለጸ ሲኾን የአፈር መሸርሸርን በማስቆም፣ የጠፉ ምንጮች እንዲፈልቁ እና የዱር እንስሳት መጠለያቸውን እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ የተፈጥሮን ትንሳኤ እውን እያደረገ መኾኑን አመልክቷል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አካባቢን ከመጠበቅ ባለፈ በቀጥታ ከኢኮኖሚ እና ከምግብ ዋስትና ጋር የተሳሰረ መኾኑ ተገልጿል። ንቅናቄው በተለይም የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸውን እንደ ቡና፣ አቮካዶ፣ ማንጎ እና ፓፓያ ያሉ የፍራፍሬ ችግኞችን መትከል ላይ ትኩረት ማድረጉ የአርሶ አደሮችን የገቢ ምንጭ ከመጨመር ባለፈ የሀገር ውስጥ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ትልቅ እምቅ አቅም ፈጥሯል።
ከዚህም በተጨማሪ ከችግኝ ማፍላት ጀምሮ እስከ ተከላ እና እንክብካቤ ባሉት ሂደቶች ውስጥ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ወጣቶች እና ሴቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል።
ይህ መርሐ ግብር ጾታ፣ ዕድሜ፣ ሃይማኖት እና ብሔር ሳይለይ መላው ሕዝብ በአንድነት ቆፍሮ እና ተክሎ የሚመለስበት፣ ኢትዮጵያውያንን በአንድ ዓላማ ሥር ያሠባሠበ ትልቅ ማኅበራዊ ክስተት እና የሕዝቡ የኅብረት እና የጽናት ጥንካሬ ማሳያ መኾኑም ተብራርቷል።
በአጠቃላይ የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ሀገሪቱ ካለችበት ፈተና ወጥታ በራሷ አቅም እና በሕዝቧ ክንድ ወደ ታላቅነት የምታደርገው ጉዞ መገለጫ ሲኾን ይህ አረንጓዴ ልብስ የምድሪቱ ውበት ብቻ ሳይኾን የነፃነት፣ የብልጽግና እና የኩራት አዲስ ምዕራፍ ነው። ዛሬ የሚያርፈው እያንዳንዱ አረንጓዴ አሻራ ነገ ለምለም እና የምትማርክ ኢትዮጵያን ለልጆች ለማስረከብ የሚገባ የማይታጠፍ ቃል ኪዳን እና ለነገው ትውልድ የሚቀመጥ ሕያው ቅርስ መኾኑም ነው የተገለጸው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየቁይ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ግንባታ ተጠናቅቋል።